ሕወሓትን አውርዶ አንኳር ፖሊሲዎቿን አዝሎ ለመዝለቅ የሚደረግ ጥረት የትም አያደርስም (ከሺፈራዉ አበበ ገሠሠ(ዶ/ር)

ለሦስት አስርተ ዓመታት ገደማ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ዕልቆ መሳፍርት የሌለው  ግፍ የፈጸመችውና  አሁንም  እየፈጸመች  ያለችውን ሕወሓት በውስጥም  በውጭም ባለው ሕዝብ መራራ ትግልና  ከኢሕአዴግ ውስጥ በሕዝቡ ላይ የሚደረሰውን  ግፍ  ማየት የመረራቸው ኃይሎች ባካሄዱት የውስጥ ትግል ተዳምሮ  ከአራት ኪሎ  በትረ መንግስት  አሽቀንጥሮ  ጠቅልላ መቀሌ እንድትመሽግ እንዳደረጋት የሚታወስ ነው።ለዉጡን ተከትሎ  ሕወሓትን ተክቶ ስልጣኑን  የጨበጠው የዶ/ር አብይን መንግሥት ሕዝቡ ሆ ብሎ ደገፈው። የደገፈበትም ዋነኛው ምክንያት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር በአቶ መለስ ዜናዊና ግብረ አበሮቹ  ተንቃ፣ ተዋርዳና፣ ተረስታ፣ የነበረችው ኢትዮጵያን  ስሟን ከፍ አድርጎ በማንሳቱ ብቻ ሳይሆን ዘረኛዋ ሕወሓት  ኢትዮጵያንና  ኢትዮጵያዊነትን ለመሸርሸርና  ለማዳከም የቀረፀቻቸውን  አንኳር  ፖሊሲዎች በማስወገድ  ሕዝብን  ከሕዝብ የሚያስተባብር፣ በዕኩልነት  ዜጎችን የሚያገለግል፣ የአገርን አንድነትን የሚያጠናክርና  በተጠና ሁኔታ የቀረበ ሕዝብ  የተወያየበትና  ይሁንታውን  የቸረው  ፍትኃዊ  የሆነ  አገራዊ  አስተዳደር ያመጣል ወይም እንዲመሰረት ያደርጋል በሚል ነበር።

ህገ መንግስቱ

ሕወሓት ኢትዮጵያንና  ኢትዮጵያውያንን  በመዳፏ ውስጥ አስገብታ በፈላጭ ቆራጭነት ለብዙ ዓመታት ለመግዛት ከቀረፀቻቸው አንኳር፣ አንኳር፣ ፖሊሲዎች ውስጥ  ዋነኞቹ  ሕገ መንግሥቱና  የክልል አወቃቀር ናቸው። ሕወሓት ሕገ መንግሥቱን የቀረፀችው አገራዊ አንድነትን አስከብራ የኢትዮጵያን  ሕዝብ  አብሮነት ለማጎልበት፣ ለዕድገትና ለብልፅግና ተባብሮ እንዲሰራ ለማድረግ ሳይሆን ከፋፍላ ለመግዛትና  ገና ደደቢት በረሀ እያለች በማንፌስቶዋ ጠላቴ ነው ብላ የፈረጀችውን  አማራውን  በተቀነባበረ  ስትራቴጂና  ስልት  የሕግ ማዕቀፍ  ሰጥታ ሁለንታዊ  በሆነ መልኩ ለማዳከምና  መቸውንም ቢሆን የፈላጭ ቆራጭ ስልጣኗን እንዳይገዳደር ለማድረግ  በማቀድ ነው። ይህንንም እቅዷን ለማሳካት የሕገ መንግስቱ  ዋነኛ መሰረት ተደርጎ የተወሰደው የሽግግሩ  ቻርተር  ሲረቅቅም ሆነ ሲፀድቅ እንዲሁም  ከዓመታት በኋላ ሕገ መንግሥቱን  በማርቀቅም ሆነ በውይይት  በማፅደቁም  ሂደት አማራው  ምንም  ሚና እንዳይኖረው ያደረገችው። የጥፋቷ  ዋነኛ  ዒላማ ያደረገችውን  አማራውን ጠቀስሁ እንጂ  የትኛውም  የኢትዮጵያ  ሕዝብ  ወኪሉን መርጦ  በሕገ መንግሥቱ  ማርቀቅም ሆነ ማፅደቅ ሂደት አልተሳተፈም። ሕዝቡ ተወያይቶበታል የተባለውም  የማርቀቁን  ሂደት በዋናነት ከመሩት ሰወች ውስጥ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ  የይስሙላ እንደነበረ  ምስክርነታቸውን  መስጠታቸው ይታወሳል።

ይህ በሕወሓት የተቀረፀው ሕገ መንግሥት ገና ከመቅድሙ (Preamble) ጀምሮ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድ ሆኖ እንዳይታይ ለማድረግ፣ እኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሎ መጀመር ሲገባው፣  ሕወሓት በተንኮል እኛ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብላ ራሷ ተደናግራ ሕዝብን ስታደናግር  አሁን ድረስ የዘለቀችው:: አንድ አገር አንድ ሕዝብ መኖሩ እየታወቀ፣  ሦስት ሺና ከዚያም በላይ ዘመናት አገረ  መንግስት መስርታ  የኖረችን  አገር፣ የተለያዩ  አገሮች በፈቃዳቸው ተጣምረው አዲስ አገር እንደፈጠሩ አድርጎም ያቀርባል። ይባስ ብሎም ኢትዮጵያን  የብጥብጥ አውድማ ለማድረግ የራስን  እድል በራስ መወሰን በሚል ያለ ቦታው በተቀመጠ መርህ ሽፋን በማድረግ የመገንጠል መብት ሰጥቷል። ይሕ የመገንጠል መብትም አብሮነትን፣ መተባበርንና  አብሮ መበልፀግን  ወይም ማደግን ሊያጎለብትና ሊያበረታታ ይቅርና  በተቃራኒው  ያለመተማመንና  የግጭት  ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።

በሕገ መንግስቱ  ውስጥ ብዙ ተገቢ ያልሆኑና አሳሪ የሆኑ አንቀፆች አሉበት:: ይህም በዝርዝር  በተለያዩ  የሕግ  ባለሙያዎች እየቀረበ ስለሆነ  መድገሙ አስፈላጊ ሆኖ አላገኘሁትም:: የፅሑፌ ዋና  ትኩረትም ይህ አይደለም። ዋናው ቁምነገሩ፣ ሕወሓት ለዚህ ሰነድ መሰረት አድርጋ  የወሰደችው የራሷን  የሕወሓትን  ማኒፌስቶና፣ የሽግግሩን  ቻርተር ሲሆን  የቀረፀችውም ሆነ ያፀደቀችው ራሷ ሕወሓት ናት። የሰነዱ ዋና መንፈስም ሆነ አላማው ኢትዮጵያን እንደ አገር ለማጠንከርና ሕዝቧን በአንድነቱ የበለጠ ለማስተሳሰር፣ በዜግነቱ በዕኩልነትና በነፃነት በየትኛውም የአገሪቱ  ክፍል ተዘዋውሮ ሰርቶ እንዲበለፅግና  ፍትሕ እንዲሰፍን ሳይሆን፣ በተንኮል የሸረበቻቸዉን መሰሪ የሆኑ ልዩ፣ ልዩ፣ ፖሊሲዎች ማውጣት የሚያስችል ፣ ከፋፍሎ ለመግዛትና ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን አገዛዟን ለማጠናከር የተዘጋጀ ሰነድ ነው። ተደጋግሞ እንደተገለፀው ይህ ሕገ መንግሥት ለሕዝብ መተዳደሪያነት ያልተጻፈ፣ ሕዝብ ያልተወያየበት፣ የማያውቀውና ያላፀደቀው፣ ከፀደቀ በኋላም ይሁንታውን  ያልቸረው፣ ያልተቀበለው፣ ሕወሓት  አስገድዳ የጫነበት ሰነድ ነው። ለዚህም  ነው የሕወሓት ሕገ መንግሥት ተብሎ ቢጠራ  ስህተት  የማይሆነው። ወደ ዝርዝር አንቀጽ ጉድለቶች  ትንታኔ አልገባም ያልሁ ቢሆንም  ሳልጠቅሰው ማለፍ የሌለብኝ  ሌላው  የሕወሓት መርዘኛ  ተንኮል መገለጫ፣ ሕዝብን ከሕዝብ በቀጥታ ለማጋጨት የቀመረችዉ ሴራ፣  በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ይኖረዋል የሚል አንቀፅ መሰንቀሯ  ነው። ታድያ አፈፃፀሙ በሕግ ዝርዝር የሚታይ ይሆናል ብትልም፣ ከአራት ኪሎ በሕዝብ ቁጣና ትግል ተባራ እስከምትሄድ  ድረስ፣ ድፍን  ሃያ ሰባት ዓመት አንዳችም የሕግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት አልደፈረችም።

ይህ አካሄድ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ከመሰረቱ  ስህተት  መሆኑን  ራሷ ሕወሓት ተረድታ አንዳንዴ  እንደ ማስፈራሪያ  ሌላ ጊዜ የፖለቲካ  ድጋፍ ለማግኘት እንደ  ማማለያ  እየተጠቀመችበት ቆይታለች። ይህ ፈጽሞ የማይታሰብና  የማይሰራ ነው:: ምክንያቱም የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን መብት የሚጥስ፣ ዜጎችን  ከዜጎች የሚያበላልጥ፣ ብሎም የመላው ኢትዮጵያ ዋና ከተማ የሆነችውን ለአንድ ማህበረሰብ ማደል ፈጽሞ የሕዝብንና  የአገርን አንድነት  የሚያናጋ  ጉዳይ ነው:: ሆኖም ግን አጎራባች መስተዳደሮች በሚያገናኟቸው ጉዳዮች እየተወያዩ የሚፈቷቸውና  አንዳንድ  የኃይል አቅርቦት፣ትራንፖርት፣መንገዶች ስራ፣ጤናና  ተፈጥሮ ጥበቃ  የመሳሰሉት  ጉዳዮች  አይኖሩም  ማለት አይደለም:: ይህ ግን የአስተዳደሮችን ትብብር የሚደነግግ ስምምምነት ማዘጋጀት እንጅ ለየትኛውም አካል ልዩ ጥቅም የሚሰጥ አይሆንም።

ይህ  ሕዝብ ይሁንታ ያልሰጠው ሕገ መንግሥት እንዲለወጥ ካልሆነም ቢያንስ እንዲሻሻል  ብዙዎች ያለማቋረጥ  ሲያነሱት የቆየ ጥያቄ ቢሆንም ፣በተለይ  አማራው:   አማራውን  ያገለለ፣ የማላውቀው  ሰነድ  በመሆኑ በአዲስ  ሕገ መንግሥት መተካት ወይንም መሻሻል አለበት  ብሎ መጠየቅ ከጀመረ ሰንበትበት  ብሏል። ነገር ግን ሕወሓት  ይህ ህገ መንግሥት መሻሻል እንዳይችል ብዙ አጥሮችን አስቀምጣለች::  በተለይም  የተንኮሏ ዋና አስኳል የሆነዉ  ኣንቀፅ ፫፱፣ ማለትም የመገንጠል መብት የሚቸረዉ፣  ሕወሓት በህይወት እስካለች  ድረስ እንዳይነካ በሚያደርግ መልኩ አጥራዋለች። ይኸውም ይህ አንቀፅ  ያለበትን ምዕራፍ ለማሻሻል የሚይቻለው  ዘጠኙም ክልሎች ይሁንታ ሲሰጡ ነው በሚል:: በዚህም ቀመር መሰረት ቢያንስ ራሷህወሓት የምትመራዉ  የትግራይ ክልል ከተቃወመ ማሻሻል አይታሰብም ማለትነዉ

የክልሎች አወቃቀር

ከሕገ መንግሥቱ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ዋነኛ የሕወሓት ሴራ፣ ጥቅሙና  ጉዳቱ  ሳይጠና ሕዝብ ሳያውቀውና ሳይመክርበት የራሷን የሕወሓትን፣  የኦነግን ና  በወቅቱ የነበሩ  ግብረ አበሮቿን አላማ ለማሳካት  ቋንቋን መሰረት አድርጎ  የተዋቀረው  የክልል አወቃቀር ነው። ሕወሓት  ይህንን ክልል ስትዘረጋ  አንደኛ፣  ከአማራው  ጉልበቷንና  ስልጣኗን  ተጥቅማ የወሰደቻቸውን እንደ ወልቃይት ጠገዴ ጠለምትና ራያ መሬቶች የሕግ ከለላ ለመስጠት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በመላው ኢትዮጵያ አገሬ ብሎ እየኖረ ያለውን አማራ እንደ ሁለተኛ  ዜጋ  ተቆጥሮ በአገር አስተዳደር ፣ በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚው  ምንም ቦታ እንዳይኖረው ለማድረግ ነው። ገፋ ሲልም፣ በተፈለገ ጊዜ ከያለበት እንዲፈናቀል ለማድረግ በማቀድ ነበር። ይህ ሴራ እስካሁን ድረስ እየተሰራበትና ያለመችውን ውጤት እያስገኘላት ቀጥሏል። ሦስተኛ፣ ክልሎችን የአንድ ብሔረሰብ  ወይም የተወሰኑ ብሔረሰቦች ባለቤትነት በመስጠት በየክልሎች የሚኖረውን  የተቀረውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአገሩ ላይ አገር አልባ በማድረግ ኢትዮጵያዊነትን  አዳክሞ  ብሔርተኝነትን ለማጎልበት ታስቦ ነው። ይህ ቋንቋን መሰረት አድርጎ  የተዋቀረ ክልል ብሔርተኝነትን  አጎልብቶ ኢትዮጵያዊነትን  እጅግ እንዳዳከመውና እንደጎዳው በግልጽ እየታየ  ነው። በዚህ አግባብ ባልሆነ  ሁኔታ የተዋቀሩ ክልሎች የየራሳቸውን ሕገ መንግስት እንዲያዘጋጁ ሲደረግ  በተቸራቸው ክልል ውስጥ አንዱን ማህበረሰብ  ባለ አገር ሌላውን  አገር አልባ አድርገው በኩራት በህግ  ደንግገው አስቀምጠዋል።

ለምሳሌ ሐረሬ ክልል ውስጥ ሌሎች ማህበረሰቦች አብላጫ ቁጥር ያላቸው ሆኖ እያለ ለአደሬው በባለቤትነት ስለተሰጠው ሌሎች ከሁሉም ነገር ተገልለው አደሬውና  ኦሮምው አዛዥና  ናዛዥ ሆነው ይገኛሉ። የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግሥት ክልሉን ለኦሮሞዎች  በባለቢትነት በመስጠቱ ከ ፩፭  እስከ ፳ ሚሊዮን የሚሆነው አማራውና  ቀሪው ኢትዮጵያዊ  ምንም አይነት መብት እንዳይኖረው ተደርጓል። በቋንቋውም ልጆቹን እንዳያስተምር ተፀዕኖ ተደርጎበታል። በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ከተሞች ውስጥ ብሄርን መሰረትያደረገ የቤት ማፍረስና የማፈናቀሉ ዘመቻ የዚህ የተንሸዋረረ የክልል ሕገ መንግሥት ቀጥተኛ ውጤት መሆኑ አያጠያይቅም። ሕወሓት፣ ከጎጃም መተክልን፣ ከወለጋ አሶሳን ቆርሳ ያዋቀረችው  ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፥  ለጉሙዝ ፣ በርታ፣ ሺናሻ፣  ማኦና ኮሞ ማህበረሰቦች ባለቤትነት በመስጠት፣ የተቀረውን የአካባቢ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ ሁሉ መብት አልባ በማድረግ በተለይም አማራውን በክልሉ መንግሥት  መዋቅር ድጋፍ በየቀኑ  እንደ በግ እያሳረዱት  ይገኛሉ። ከዚህ  ክልል የተፈናቀለዉ በጣም ብዙ ሲሆን ትክክለኛ ቁጥሩ አይታወቅም። ይህ  ያለ ሕዝብ ይሁንታ በሕወሓትና ኦነግ ሴራ የተዋቀረ ክልል አብሮ የኖረውን ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዲተላለቅ አድርጎታል። መሬት ይገባኛል የማይባባል ጎረቤታም  ክልል የለም።ለምሳሌ ሶማሌ ክልልና ኦሮሚያ፣ ሲዳማና ኦሮሚያ፣ አማራና  ትግራይ፣ አፋርና  ትግራይ፣ አማራና  ቤኒሻንጉል፣ ኦሮሚያና በኒሻንጉል፣ ሶማሌና  አፋር፣ አማራና ኦሮሚያ፣(በደራ ማንነት) ደቡብ ክልልና ኦሮሚያ (ጌዶና ጉጂ) በመሬት ውዝግብ ላይ ይገኛሉ። ክልልሎች ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ ዜጋ በዕኩልነት መኖር የማያስችሉ ከመሆናቸዉም አልፎ  ለዜጎች  በሚሊዮኖች  ከቀያቸዉ መፈናቀል ዋነኛ ምንጭ  ሆነዉ  ይገኛሉ:: ኦሮሞዉ ከሶማሊያ  ክልል እንዲሁም  የጌዶን  ህዝብ በሚሊዮኖች መፈናቀል መፈናቀል ማስታወስ ይቻላል::

የዶ/ር አብይ መንግሥት ስልጣን ከያዘ በዚህ ሁለት አመት ጊዜ ውስጥ እንኳን ፪.፭ ሚሊዮን የሚሆኑ  ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።ይህ  የአገር ውስጥ መፈናቀል፣ (internal displacement) ኢትዮጵያን፣ በጦርነት ይታመሱ ከነበሩት ሶሪያና  ከየመን አልፋ ከዓለም በአንደኛ ተርታ እንድትሰለፍ  አድርጓታል። ባለፈው ጥቅምት ወር፣ በኦሮሚያ  ክልል ኦርቶዶክስ  ክርስቲያኖችንና  አማራውን  ኢላማ  ያደረገው ጭፍጨፋና  ለ ፰፮ ኢትዮጵያውያን  በአሰቃቂ  ሁኔታ መገደል ምንጩ  ይኸው የክልል አወቃቀር  የፈጠረው የዘረኝነት  መንፈስ ነው። ይህ  የክልሎች ሕገ መንግሥት የሰው ልጅ መብትን ያማያከብር፣ የዜጎችን እኩልነት የማያረጋግጥና  ፍትኅዊነት የጎደላቸው በመሆናቸው፣ ኢትዮጵያ  የፈረመችውን  የዓለም አቀፍ የሰው ልጅ መብት ድንጋጌዎች የሚፃረሩ  ብቻም ሳይሆን፣ ሕወሓት ካዘጋጀችው የአገሪቱ  ሕገ መንግሥት ጋርም እንኳ ይቃረናሉ። እንደሚታወቀው አሁን ባለው ሕገ መንግሥት ውስጥ  የሰዉ ልጆች መብትን ማክበር በተመለከተ የዓለም አቀፍ ሕግ አካል የሆኑ ብዙ አንቀፆችን አካቷል:: ይህ ግን የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ  ለማደናገሪያነት ታስቦ  የተካተተ  እንጂ አንዲትም  ቀን ተግባራዊ ሆኖ እንደማያውቅ በግልጽ ይታወቃል። አሁንም በዚያው በነበረው ተቃርኖ እንደቀጠለ ነው።

 

             ምርጫዉን ማራዘምና ህገ መንግስቱ

የዚህ  ሁሉ መፍትሔ በሕወሓት  መርዘኛ ሴራ የተፈጠረውን  ህገ መንግስት  በአዲስ ሕዝብ በመከረበት ህገ መንግሥት መለወጥ ነው የሚሉ በርካታ ድምጾች እንዳሉ ሁሉ  እንኳን አዲስ ሕገ መንግሥት ይቅርና በሕገ መንግሥቱ አንደራደርም፣ ምንም እንዲሻሻል አንፈልግም የሚሉ  የበረቱ  ድምጾች ከራሷ ከሕወሓት ብቻ ሳይሆን ከዶ/ር አብይ  መንግሥትም በኩል ሲደመጥ መቆየቱ ገራሚ ነገር ከመሆኑም አልፎ የሰው ለውጥ ነው እንጂ የምር ለውጥ አልመጣም የሚል የሰላ ትችት መቅረቡ ተገቢ ነው ማለት ይቻላል።

ታዲያ መቸም  ኮሮና (Covid-19) ያላመጠው ነገር የለምና ሕገ መንግስት አላሻሽልም፣ ምርጫ አላራዝምም ሲል የነበረው የዶ/ር አብይ መንግሥት፣ በሁኔታው ተገዶ ምርጫ ማራዘም እንዳለበት ሲወስን፣ መካሄድ የሚችለው የመንግሥቱ  የስልጣን  ዘመን ከሚያበቃበት ከመስከረም ፴፣ ፳፩፫ ዓ/ ም በኋላ በመሆኑ፣ እስከ ምርጭው ድረስ ሕጋዊ ስልጣን ይዞ ለመቀጠል የሚያስችሉትን መውጫ ሕጋዊ መንገዶች ሲያፈላልግ ቆይቶ ከአቀረባቸው አራት አማራጮች ውስጥ ሕገ መንግሥቱን ማስተርጎም የሚለውን በመምረጥ ይህን በፓርላማው  አጸድቆ ወደ ተርጓሚው አካል ልኮታል። እዚህ ላይ ሕገ መንግሥቱን የሚተረጉም የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት (Constitutional Court or Supreme Court) እንዲኖር አለመደረጉ ሌላው የሕገ መንግሥቱ  ዋነኛ  ክፍተት ነው። የዶ/ር አብይ አስተዳደር የራሱን አማራጭ  ከወሰነ በኋላ ለይስሙላ የተወሰኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለመወያየት ሳይሆን ለማሳወቅ መጥራቱ ትክክል አይመስለኝም። መሆን የነበረበት፣ ይህን የመሰለ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ ላይ ለመምከር እንኳንስ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይቅርና የሲቭል ማሕበራትም ሆነ የታወቁ ምሁራንና  ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በሰፊው በማሳተፍ ተቀባይነት ያለው የአገርን ደህንነት ሊያስከብር የሚችል ዘላቂ መፍትሔ መሻት ይገባ ነበር። ምርጫው መራዘሙ የግድ ነው። ይህ ሊያከራክር የሚችል ጉዳይ አይደለም። የኮረና ወረርሽኝ ከመምጣቱ በፊት ምርጫው ተራዝሞ ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታዎችና ተቋማት ላይ ይሰራ፣ ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል የሚሉ የተጠናከሩ ጥያቄዎች በብዙዎች ተጠይቆ ነበር። ስለዚህ፣ የምርጭውን መራዘም አብዛኛው ሕዝብ የሚደግፈው ጉዳይ ነበር፣ አሁንም ይደግፈዋል።

ዋናው ጥይቄ ግን ያለው መንግሥት የስልጣን ዘመን ከሚያበቃበት እስከ ምርጫ ጊዜ የሚያስተዳድረውን መንግስት ጉዳይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ስምምነት የተደረሰበት መሆን ነበረበት ነው። ይህን አስመልክቶ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዴት መፈታት እንዳለበት የየራሳቸውን የመፍትሄ መንገድ እያቀረቡ ይገኛሉ። ከቀረቡት ሃሳቦች ውስጥ በጥቅሉ የሽጝር መንግስትይቋቋም፣ የባለሞያዎች: ባለ አደራ መንግሥት ይቋቋም የሚሉና ያለው መንግሥት እስከ ምርጫው ድረስ ይቀጥል የሚሉና ሌሎችም የመፍትሔ ሃሳቦች ተንጸባርቀዋል። አገራችን ኢትዮጵያ በውስጥም ሆነ በውጭ ኃይሎች ውጥረት ውስጥና የህልውና አደጋ ተጋርጦባት ባለበት ወቅት፣ ለአዲስ መንግሥት ምስረታ በመራኮት ክፍተት ከመፍጠር አሁን ያለው መንግሥት ከነ ጉድለቱ ቢቀጥል፣ ከቀረቡት አማራጮች ሁሉ የተሻለው ነው ብየ አምናለሁ። ነገር ግን  ዝም ብሎ ይቀጥል ሳይሆን; ምን ለመስራት ነው የሚቀጥለው?ለምን ያህል ጊዜ ነዉ የሚቀጥለው?  የሚሉት ጥያቄዎች ተገቢ መልስ ማግኘት አለባቸው። ኢትዮጵያ  ልታልፈው የማይገባ ወርቃማ እድል እንደገና  አግኝታለች ብየ በፅኑ አምናለሁ። ይኸውም ወያኔ አማራውን ለማድቀቅ፣ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በዘር ከፋፍላ አምባገነን አገዛዟን ለማደራጀት አቅዳ የቀረጸችው ሕገ መንግሥትና  የኢትዮጵያውያን  የሞት ፋብሪካ የሆነዉ የክልል አወቃቀር መለወጥ ያለበት አሁን ነው። ፌደራሊዝምን  የተቃወመ  የለም። እየተጠየቀ ያለው የሕዝብ አንድነትን፣ የአገር ብልጽግናን ሊያረጋግጥ የሚችል ሕዝብ የመከረበት፣ ባለሙያዎች ያረቀቁት ሕገ መንግሥት ይዘጋጅ፣ ክልል ፈርሶ ሁሉንም የፌደራል መርሆዎች በመጠቀም በተዋቀረ፣ ሕዝብ ይሁንታ በሰጠው የፌደራል ክፍለ ግዛቶች ይተካ ነው። ይህ ማንንም በተለየ  ሁኔታለመጥቀም ወይም ለመጉዳት ያለመ አይደለም። ሁሉንም እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ እንጂ:: እነዚህን ሁሉ አብይ አገራዊ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ ለማድረግና ነፃ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ አገራዊ ተቋማትን ለመመስረትና ለምርጫው ለመዘጋጀት ቢያንስ ሁለት ዓመት ስለሚያስፈልግ፣ የዚህ ያለው መንግሥት የስራ ዘመን  ለሁለት ዓመት ቢራዘም የተሻለ ነው።

የመንግሥት ቀጣይ ስልጣን  ለስንት ጊዜ ይራዘምና በተራዘመው ጊዜ ውስጥ ምን፣ ምን፣ ታላላቅ አገራዊ ጉዳዮች ትኩረት ተ ሰጥቶ መሰራት አለበት የሚለውን ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሁሉም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቶ አብዛኛውን የሚያግባባ አገራዊ አጀንዳ ይዞ መውጣት በእጅጉ ያስፈልጋል። ለአገር ይጠቅማል ብለው የሚያስቡትን የመፍትሔ ሃሳብ ሁሉ ተቃዋሚዎችም ሆኑ ሌላው በነፃነት እንዲያቀርቡ መንግሥት ማበረታታ አለበት። ይህ የተገኘውን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

 

 

በሚራዘመዉ የስልጣን ዘመን መንግስት ምን ይስራ

በእኔ አስተያየት በሚራዘመዉ የሁለት አመት የስልጣን ዘመኑ መንግስት የሚከተሉትን አብይ አገራዊ ጉዲዮች ቢያከናዉን የሚፈለገዉን ዉጤት ለማምጣት ያስችላል ብየ አምናለሁ::

፩. ህገ መንግስቱን የታወቁ የህግና ሌሎች መሰል ባለሙያዎች ባረቀቁት፣ ህዝብ በመከረበትና በወኪሎቹ በኩልና በራሱም ቀጥተኛ ተሳትፎ ባፀደቀዉ በአዲስ ህገ መንግስት ፣ እንዲለወጥ ማድረግ

፪. ክልሎችን በማፍረስ ሁሉንም የፌደደራሊዝም መርሆዎች መሰረትአድርገዉ በሚቋቋሙ በአዲስ የፌድራል ክፍለ ግዛቶች ማዋቀር

፫. ነፃና  ፍትኅዊ  ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ የህግና አስተዳደራዊ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት

፬. የተጠናከረና ገለልተኛ  የምርጫ ቦርድና ምርጫ ሂደቱን የሚመሩ አካላትን ማቋቋም

፭.የፍትኅ ስርአቱ ነፃነቱን ጠብቆ ሊሰራ የሚችልበት አቅም መፍጠር

፮. የፖለቲካ ፖርቲዎች ፣ የሲቪክ ማህበራትና ሚዲያዉ ያለ ተፅዕኖ እንዲሰሩ ማስቻል

፯. በፀታ አስከባሪዉና መከላከያዉ ላይ ተቀባይነት ያለዉ ሪፎርም ማካሄድ

፰. የክልሎች ልዩ ሃይልና ፀረ ሺምቅ ኃይል ወደ ፖሊስና መከላከያ የሚቀላቀልበበትን ሁኔታ ማመቻቸት

፱. ትክክለኛና ተዐማኒነት ያለዉ የህዝብ ቆጠራ ማካሄድ

፲. የትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት

          ወቅታዊዉ የአገር ኅልዉና ፈተና

አገራችን ከመቸውም ጊዜ በበለጠ በውጭ ጥንተ ጠላቶች ልትጠቃ የምትችልበት አጋጣሚ በጣም ከፍተኛ ነው። በአገር ውስጥም ስልጣኑን ያጣው ኃይል አጋራቸው የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው። ሱዳን አጋጣሚውን ተጠቅማ የኢትዮጵያን ደንበር ዘልቃ በወረራ መሬት ከያዘች ወራት ተቆጠሩ:: በህዳሴ ግድብ ቆሽቷ ያረረው ገብጋባዋና እኔ ብቻ ልብላ ባይዋ  ግብፅ ብዙ ሴራ እያሴረች መሆኑ ግልጽ ነው። የሱዳን ድንበር ዘልቆ መግባትም ከዚህ የግብፅና  ግብረ አበር የአረብ አገሮች አይዞሽ  ባይነት  የመጣ መሆኑ አያጠያይቅም። ስለዚህ የኢትዮጵያውያን   ምላሽ መሆን ያለበት በህብረትና በአንድነት  በመሰለፍ  ድንበር ጥሶ የገባዉን  ማስወጣት፣ ግድቡን  በትጋት መጠበቅና ስራውን በተገቢው መልኩ እንዲከናወን ማድረግ ነው። የግብፅን  ዓለም አቀፋዊ  የተሳሳተ መረጃ  ማሰራጨት ዘምቻ ሊያመክን የሚችልና እውነቱን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያስጨብጥ የዲፕሎማሲ ዘመቻም  የኢትዮጵያውያን   ምላሽ አንዱ አካል መሆን ይኖርበታል።

ይህንን የመሰለ አገራዊ አንድነት ለማምጣት ከመንግስት ብቻ ሳይሆን ከተቃዋሚዎችም  የሚጠብቅ ይሆናል:: ዋናው ድርሻ ግን የመንግሥት ይሆናል። ለሁሉም፣ ለአገር ህልውና ሲባል የፖለቲካ  ቅንነትና ግልጽነት ከሁሉም አካል ይጠበቃል። በተለይ ከመንግሥት:: የአገር ህልውናን በማረጋገጥ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ መዘጋጀቱ አይነተኛ ተመራጭ መንገድ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ በኋላ በሽንገላና በብልጣ ብልጥነት ተመርጫሎህ ብሎ ያለ ነፃና ፍትሐዊ  ምርጫ የሚመጣን  መንግሥት  ታግሶ  የሚቆይበት ዕድሉ የተሟጠጠ ነው። ስለዚህ  ነፃና  ፍትሐዊ  ምርጫ ለማካሄድ መሰረት የሚጥለውን  የሕገ መንግሥት  ለውጥ ካልተቻለም  ትርጉም ያለው ማሻሻል ለማድረግና  ክልሎችን አፍርሶ በሌላ ተቀባይነት ባላቸው የፌደራል ክፍለ ግዛቶች ለመተካት  ሁሉም ቆርጦ መስራት አለበት። አለበለዚያ ሁሉንም  ዜጋ በእኩልነት  የማያስተናግድ  የፌደራል ሕገ መንግሥት፣ የክልል ሕገ መንግሥትና  የክልል መዋቅር ይዞ ነፃና ፍትሐዊ  ምርጫ አካሄዳለሁ፣ ዲሞክራሲያዊ  ስርዐት እገነባለሁ ማለቱ  በሕዝብ ላይ መቀለድ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም፣ ለዜጎች የተበላለጠ  መብት የሚሰጥ  የአፓርታይድ  አገዛዝ  እንጂ  ዲሞክራሲያዊነት  ስላልሆነ::

ለማጠቃለል፣ የኢትዮጵያ  ሕዝብ ሕወሓትን አምርሮ የጠላትና የታገላት  ትግሬዎች በመሆናቸው ሳይሆን ይዘውት በመጡት የዘረኝነት፣ የመለያየትና  የአድሏዊነት አሰራር ነው። እነዚህ ባህሪዎች ደግሞ በዋነኛነት የተንጸባረቁት በሕገ መንግሥቱና  በክልል አወቃቀሩ  ነው። ታዲያ  ሕወሓትን  ከአራት ኪሎ  አባረን  መቀሌ እንድትመሽግ አድርገናታል ብሎ  መመጻደቁ ፍሬ ሊኖረው የሚችለው  አገርን አስማምቶና  አስተባብሮ ለማስተዳደር ሳይሆን  በተንኮልና  በሴራ ሕዝብን ከሕዝብ  ነጣጥሎና፣ በአምባገነንነት ከፋፍሎ፣ ለመግዛት፣ የተቻላትን ሁሉ የአገር አንጡራ ሀብት ለመዝረፍ እንዲመቻት  ያስቀመጠቻቸውን እኒዚህን  ከላይ  በተደጋጋሚ የተጠቀሱትን አንኳር ፖሊሲዎቿን  በመለወጥ ይሆናል። በተጨማሪም  የትግራይ ህዝብ በምን እዳዉ ነዉ ድፍን የኢዮጵያን ሕዝብ ሲያሸብር የኖረን  ህዋሓትን  የመሰለ አረመኔ  የማፍያ  ቡድን(በተለይም የበላይ አመራሩ)ጫንቃዉ ላይ ተሸክሞ እንዲኖር  የተፈረደበት:: መፍትሄዉ የትግራይ ህዝብ  ህወሓትን ለማስወገድና ወንጀለኞቹን ለፍርድ ለማቅረብ የጀመረዉን ትግል  በተጠናከረ መልክ መደግፍና ለዉጤት እንዲበቃ ማድረግ ነዉ::

እነዚህን  የአገር  አንድነት፣ የሕዝብ  እድገትና  ብልፅግና  ፀር የሆኑትን  የተወሳሰቡ  የሕወሓትን  ፖሊሲዎች  ሳይለወጡና  ህወሓትን ከትግራይ ህዝብ ጫንቃ ሳያወርዱ መቀጠል የትም እንደማያደርስ በመገንዘብ፣ መንግሥት በሚኖረው የስልጣን  ዘመኑ እርምጃ እንዲወስድበት ጥሪ አቀርባለሁ። ጊዚያዊ  ስልጣንን ከማደላደል  ይልቅ ለአገርና ለሕዝብ  የሚበጀውዉን  ሠርቶ  የማይጠፋ  ስም ጥሎ  ማለፍ  የተሻለ መሆኑ በዘመናት  የተረጋገጠ  ሀቅ ነው።