መንግስት ከደምቢ ዶሎ ዩንቨርሲቲ በታገቱት ተማሪዎች ዙሪያ መረጃ እየሰጠው ባለመሆኑ ምርመራ ሊጀምር መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ

መንግስት ከደምቢ ዶሎ ዩንቨርሲቲ በታገቱት ተማሪዎች ዙሪያ መረጃ እየሰጠው ባለመሆኑ ምርመራ ሊጀምር መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ❗️

ከአምስት ወራት በፊት ነበር በደንቢዶሎ ዩንቨርሲቲ በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት በጋምቤላ በኩል አድርገው ወደ ቤተሰቦቻቸው በመጓዝ ላይ ያሉ የዩንቨርሲቲው ተማሪዎች ባልታወቁ ሰዎች መታገታቸው የተሰማው። ከዚያ ጊዜ አንስቶም ህዝቡ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በተናጥል እና በሰላማዊ ሰልፎች ተማሪዎቹ እንዲለቀቁ ጥያቄ ሲቀርብ ነበር።

ዘግይቶም ቢሆን መንግስት ተማሪዎቹ መታገታቸውን የተወሰኑትንም ማስለቀቁን እና ቀሪዎቹን ለማስለቀቅ ስራ መጀመሩን ቢናገርም እስከ አሁን ድረስ ተማሪዎቹ አለመለቀቃቸውን ወላጆቻቸው ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል። ወላጆቹ እንደነገሩን ከአማራ ክልል ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ድረስ የልጆቻችንን ጉዳይ እንዴት አደረጋችሁት ብለን ስንጠይቅ ከበር ይመልሱናል ሲሉም ተናግረዋል።

የልጆቻችንን መታገት ስራዬ ብሎ የሚከታተል አካል የለም ያሉት እነዚህ ወላጆች ስራችን ሁሌ ለቅሶ እና ሰቀቀን ብቻ ሆኗል ብለዋል። አሁን ላይ ስለልጆቻችን ስናነሳ ያልተገባ እና ነውረኛ ጥያቄ ያነሳን የሚመስላቸው የመንግስት ተቋማት አሉ ይህ መሆኑ በህመማችን ላይ ተጨማሪ ስቃይ ፈጥሮብናል ሲሉም ወላጆቹ አክለዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም የወላጆቹን ጥያቄ ይዞ የሚመለከታቸውን የመንግስት ተቋማት የጠየቀ ሲሆን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ እየሰጠን አይደለም ብሏል። መንግስት በታገቱት ተማሪዎች ዙሪያ መረጃ እየሰጠን ባለመሆኑ ምክንያትም ኮሚሽኑ ለብቻው አዲስ ምርመራ ሊጀምር መሆኑን በኮሚሽኑ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ አማካሪ ራኬብ መሰለ ተናግረዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም እገታው ከተፈጸመበት ከኦሮሚያ ክልል መንግስት አንስቶ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ድረስ ያሉ የመንግስት ተቋማትን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

ETHIO-FM

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *