ችግኝ ተክሎ፣ ሰው የሚነቅለው መንግሥት እና “ሥራ ፈቱ” ባልደራስ!

ተፈጥሮ ዑደቷን ጠብቃ እየሄደች ነው። ብርሀን በጨዋ ደንብ ለጨለማ ቦታዋን ለ’ቃለች። እንስሳትም በየጎሬያቸው ገብተዋል። አዕምሮን የሚያድሰው የወፎች ዝማሬም አሁን የለም። «ጊዜ ለኩሉ» እንደተባለው ሲንጫጫ የዋለው ዓለም ፀጥ፣ ረጭ ብሏል። በለበሰው ስጋ ምክንያት ድካም ባህሪው ነውና፣ የሰው ልጅም ተዘርሯል። ውድቅት ሌሊት ነው።

በኑሮ ውጣውረድ ሲዳክር የዋለው ይህ ግለሰብ፣ የሞት ታናሽ ወንድም በሆነው እንቅልፍ ተወስዷል። ምን ዋጋ አለው! ስልኩ በተደጋጋሚ መጥራት ጀመረ። «የተኛ በጩኸት መነሳቱ አይቀርምና» ከጣፋጩ እንቅልፍ እንደምንም ነቃ። በብርቱ ድካም ውስጥ ሆኖ፣ አይኑን በቅጡ ሳይገልፅ፣ መብራት ሳያበራ፣ ስልኩን በዳበሳ አግኝቶ፣ አነሳው። «ሄለው!» አለ። አንዲት ምስኪን ሰው ታለቅሳለች። ስቅስቅ እያለች።

«እባክህን ድረስልን፣ ቤት እያፈረሱብን ነው፣ የመንግስት ሰዎች ናቸው፣ እያፈናቀሉን፣ እያዋከቡን ነው፣ ወዴት እንሂድ? ምንስ መድረሻ አለን? ድሀ መኖር አይችልም ወይ? ሀገራችን አይደለም ወይ? ህፃናት አሉ፣ እርጉዞች አሉ፣ አራሶች አሉ፣ አረጋውያን አሉ፣ ህሙማን አሉ፣ ምን ይዋጠን? ስለፈጠራችሁ ድረሱልን» ይላል ከስልክ ማዶ ያለው የስቃይ ድምፅ።

ከእንስቷ ድምፅ በተጨማሪ የህፃናት፣ የአዛውንቶችና የሴቶች ለቅሶም ቀልጧል። ግለሰቡ ከምድር ሲኦል ተደውሎ፣ ከጥልቅ እንቅልፍም ተነስቶ የሚሰማው ሲቃ በህልሙ እንዲሆን ተመኘ። ነገርየው ግን ቅዠት ሳይሆን በገሀዱ ዓለም እየሆነ ያለ እውነታ ነበር። ለዛውም በመንግስት ሹማምንት አቀናባሪነት የሚፈፀም ወከባ። በራሱ ካልደረሰ በስተቀር መሃል ኢትዮጵያ፣ አዱ ገነት ውስጥ ይህ ይሆናል ብሎ ማን ያምናል? ህዝቡ በመዓልት በየቴሌቬዥኑ ዘይትና በሬ ሲያከፋፍሉት፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በየፎቶው ጤፍ ሲሸከሙለት የሚውሉ መሪዎቹ፣ በለሊት እንዲህ ያደርጉታል ቢባል ማንስ ይረ’ዳል?

አይደለም ከእንቅልፍ ከሞት የሚቀሰቅሰው የሴትዮዋን መልዕክት፣ በተሻለ ንቃተ ህሊና ማስተናገድ ጀመረ። መብራቱን አበራ፣ ቆሞ ወዲያና ወዲህ እየተንቆራጠጠ ማን ልበል? ከየት ነው? ምን ተፈጥሮ ነው?….ጥያቄውን ያዘንባል።

ወንድሜ በጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ የነበርከው ከላይ ያለው ሰው አንተ ሁንና፣ ይህ ስልክ የተደወለው ወደ አንተ ቢሆን ተመልሰህ ትተኛለህ? ወይስ ምን ታደርጋለህ? የህሊና ፍርድ ፍረድ!

መሰል የስልክ ጥሪዎች፣ አሁን አሁን ጊዜ ለባልደራስ አመራሮች የተለመደ እየሆነ መጥቷል። ዜጎች አንዳች ተዓምር የምትፈጥርላቸው ይመስል፣ ከለሊቱ 9 እና 10 ሰዓት ደውለው “ድረሱልን” ይሉሀል። በስልክ ያነባሉ። ደረት ይ’ደቃሉ። ብሶታቸውን ማሰማት ያለባቸው ወደ መንግሥተ መስሪያ ቤት ሄደው መሆኑን ዘንግተው አይምሰልህ፣ ገና ስልጣን ያልያዘው ባልደራስን መምረጣቸው። ቢያንስ ወደ ተጎዱበት ቦታ ሄዶ አብሯቸው ያለቅሳል። አብሯቸው ያዝናል። አብሯቸው ይተክዛል። አይዟችሁ ይላል። ሰሚ ባይኖርም፣ ቢያንስ ጉዳዩን ወደ አደባባይ ያወጣል። በዚህም ይፅናናሉ። ቢያንስ «ወገን አለን፣ ሰው አለን» ብለው ለጊዜውም ቢሆን እንባቸውን ያብሳሉ። ሀዘንን መጋራት ሰውኛ ነውና፣ ይረጋጋሉ።

ክርክሩ ህጋዊ ናቸው አይደሉም? ከዚህ ብሄር ናቸው ወይስ ከዚያ ብሄር፣ መጤ ናቸው ቋሚ ነዋሪ? የሚል አይደለም። በፍፁም። «የቫይረስ ወረርሽኝ የሰው ልጅን ህይወት ስጋት ላይ በጣለበት፣ ከቤት አትውጡ በሚባልበት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዐዊና የጤና ተቋማት ጦርነትንና መፈናቀልን በሚያወግዙበት በዚህ አስቸጋሪ ሰዓት፣ ሸራ እንኳ ወጥረው ያሉ ወገኖችን መንካት ለምን ያስፈልጋል?» ነው ጥያቄው።

የነገሩ መነሻም መድረሻም፣ «ለምን ሁላችንም ሙሉ ትኩረታችንን ወደ ወረርሽኙ አድርገን፣ ከበሽታው ከተገላገልን በኃላ ምናልባት፣ አሁን ያለንበትን ግርግር በመጠቀም በህገ ወጥ መንገድ መሬት የወረረም ካለ የዛኔ ለምን በህግ አግባብ አይታይም? ለምን አሁን ላይ ትልቅ አጀንዳ ሆነ? አጀንዳ ከሆነስ ችግኝ የሚተክል መንግሥት ሰውን የሚያህል ፍጡር ከመኖሪው መንቀል ለምን ቀለለው? ነው፣ ጥያቄው። ለመሆኑ ከሰውና ከችግኝ ማን ክብር ይገባዋል? ሙግቱ’ኮ ሀገር የምትለማው ቀንቀን ችግኝን ውሀ እያጠጡ፣ በውድቅት ሌሊት የዜጎችን ተስፋ በማድረቅ ነው ወይ? ነው!?

ለፖለቲካ ፍጆታ ቢሆን ኖሮ፣ ባልደራስ አንድ ቦታ ላይ ብቻ በመገኘት ይህን እኩይ ተግባር አጋልጦ ዝም ማለት በቂው ይሆን ነበር። እንደሌሎቹ ለማዳ የቤት ውስጥ ተቃዋሚ¡ ፓርቲዎች «አይኔን ግንባር ያድርገው፣ አላየሁም አልሰማሁም ወይም በለውጥ ጊዜ ነውጥ የተለመደ ነው» ብሎ ችላ ማለትም ይቻል ነበር። ግን ድህነት በዚህ፣ ፖለቲካው በዚያ የሚያላጋውን ምስኪን ሰው እያለቀሰ ድረስልኝ እያለ፣ ያውም በዚህ ፈታኝ ሰዓት፣ በፆም ወቅት፣ አስችሎህ ዝም ካልክ፣ መልሶ እንቅልፍ ከወሰደህ፣ ወንድሜ «ሰው» መሆንህን መጠራጠር የምትጀምርበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ነህ ማለት ነው። የሰው እንባ ከፖለቲካ በላይ ነውና። የምስኪኖች፣ የተገፉ ሰዎች እንባ የሚፈሰው ወደምድር ሳይሆን፣ ወደ ሰማይ ነውና።

ባልደራስ ይህን ማድረጉ በጥቂቶች ዘንድ እንደ «ስራ ፈት» አስቆጥሮታል። ወዳጄ ስብስቡ እንደ ፓርቲ የactivisim እና የintellectualization ስራውን በሚገባ እየሰራ፣ የዜጎችን እንባ ማበሱን ይቀጥላል። የስራ መፍታት ትርጉም «ከዜጎች ጋር ቁጭ ብሎ ሀዘናቸውን፣ ጭንቀታቸውን መጋራት እና ለሀገር ታሪክና ቅርስ መቆርቆር» ከሆነ፣ ፓርቲው ከዚህም በላይ «ስራ ፈት» ለመሆን ጠንክሮ ይሰራል።

ዶ/ር መክብብ ፈቀደ:
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *