ኦሮሚያ ተብሎ በሚጠራው ክልል፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ፣ በሀረር እና በድሬዳዋ በንጹሃን

ኦሮሚያ ተብሎ በሚጠራው ክልል፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ፣ በሀረር እና በድሬዳዋ በንጹሃን
አማሮችና ጉራጌዎች ላይ የሚደረገው የዘር ማጥፋት ወንጀል ባስቸኳይ እንዲቆም
እንጠይቃለን!
የአርቲስት ሓጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ ሁከት እና ብጥብጥ በኢትዮጲያ የተፈጠረ ሲሆን፤ አሁንም ከጉዳዩ ጋር በምንም
መልኩ ግንኙነት የሌላቸው ንጹሃን ዜጎች እየተገደሉ ነው! ከነዚህም ውስጥ በአንድ ምሽት ሙሉ ቤተሰብን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደል፤
የአንድን አካባቢ ሰፈር በማንነት በመፈረጅ ዜጎችን መግደል፣ መኖሪያቸውን ማቃጠል፣ ማንነታቸው አማራ ወይም ጉራጌ ናቸው ያሏቸውን
ከቤት በማውጣት በመንገድ ላይ እየጎተቱ መግደል፣ ሃብት ንብረታቸውንም ሙሉ በሙሉ ማውደም እስካሁን ከተዘገቡት ግፎች ውስጥ
ናቸው። ይህ ጥቃት በፍፁም በተገደለው አርቲስት ምክንያት ብቻ ነው ብለን አናምንም፤ ከዚህ በፊት የብጥብጡ ሁሉ ፊታውራሪ የሆነው
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ የቀድሞ አስተዳዳሪ የነበረው አቶ ጃዋር መሀመድ “ጠባቂዎቼ ሊነሱብኝ ነው” ብሎ በላከው መልዕክት ምክንያት
ከ86 በላይ ሰዎች በድንገት በየቦታው በፈነዳው አመጽ ሊገደሉ ችለዋል። ይህ እየተለመደ የመጣው ምክንያት እየፈለጉ ዘር ተኮር ጥቃት
በማድረስ እራሳቸውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብለው የሚጠሩ ቡድኖች እና ደጋፊዎቻቸው ከሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች በዋነኝነት አማራን
ቀጥሎም ጉራጌንና ማንኛውም ከኦሮሞ ውጭ የሆነ ማንነት ያለውን ሰው ጨርሶ ማጥፋት፤ ሊፈጥሩት የወጠኑትን እራሱን የቻለ አገር
እውን ለማድረግ እንደ አንድ ደረጃ ስለሚያዩት በተደጋጋሚ የሚያደርጉት ድርጊት መሆኑን ተጠቂዎቹም፣ መንግስትም፣ የአለም አቀፍ
መንግስታትም ሊገነዘቡት ይገባል!
በቀላሉ ይህ ማለት ከአሁንም በኋላ በማንኛውም መንገድ ይህ ብጥብጥ ጋብ ቢል ሌላ ተመሳሳይ ሁኔታዎችን ራሳቸው እየፈጠሩ የዘር
ማጽዳት ስራቸውን እንደሚቀጥሉ ሁሉም ወገን ሊገነዘበው ይገባል! የዚህ ብጥብጥ ዋና አስፈጻሚዎች የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አብዛኛዎቹ
አንጃዎች፣ በይፋ ኦሮሚያ ብለው የሚጠሩትን ቦታ ለመገንጠል የበላይ “ሕገመንግስቱ” በህዝበ ውሣኔ መገንጠል በሚፈቅድበት አገር ላይ
በብረት ትግል ለመገንጠል የሚታገለው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ የኢትዮጲያ ታሪካዊ ተቀናቃኝ በሆኑ አገሮች የሚረዱ ሚዲያዎችና
ራሳቸውን የፖለቲካ አንቂ ብለው የሚጠሩ እንደ አቶ ጃዋር መሃመድ፣ ፕሮፌሰር ህዝቄል ገቢሳ፣ አቶ ጸጋዬ አራርሳ፣ እና ሌሎችም በማሕበራዊ
ሚዲያው ብዙ ተከታይ ያላቸው ግለሰቦች፣ ከሁለት አመት ወዲህ ከማዕከላዊ መንግስት የተገለለው የትሕነግ ባለስልጣናት እና ካድሬዎች
እንዲሁም በነሱ የገንዘብ እርዳታ የሚንቀሳቀሰው የኩሽ ሚዲያ ኔትዎርክን ያካትታል። ይህ መላምት ሳይሆን እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት
አካላት በሚጠቀሙበት ማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ በቀጥታ በራሳቸው ንግግር አለበለዚያም ደግሞ ጥላቻን የሚያስተጋባ መልዕክቶች
ተጋርተው በተጨባጭ ስለታዩ ነው። ነገም አንድ ወንጀለኛ ተነስቶ ጥቃት ሊድርስብኝ ነው ቢል ወይንም ሌላ ወንጀለኛ ተነስቶ የራሱን
ወገን ቢገድል በጅምላ የሚረሸነው “ነፍጠኛ” ተብሎ የተፈረጀው የአማራው ማኅበረሰብ ነው።
ከላይ የተጠቀሱት ቡድኖች ሚና እንዳለ ሆኖ እስካሁን የደረሱት ጥፋቶች በዋናነት በመንግሥት አቅመቢስነት ወይንም ድብቅ ፍላጎትም
ነው። መንግሥት በበኩሉ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታም አለበት! አንድ መንግሥት እንደ መንግሥት ለመቆም
እጅግ በጣም በትንሹ ማሟላት ያለበት ጉዳይ ዜጎች በአገራቸው በሰላም ወጥተው የመግባት መብታቸውን ማስጠበቅ መቻል ነው።
እንኳንስ በአገራቸው ወስጥ የሚኖሩ ዜጎች ይቅርና በጥገኝነት የሚኖር አንድ ሰው እንኳን አንድን አገር ከረገጠ እና እራሱን ለመንግስት
አካል ካሳወቀ ሕጋዊ ከለላ ይሰጠዋል። ማንም ተነስቶ አይገለውም አያጠፋውም። በአገራችን በኢትዮጵያ በተለይም ኦሮምያ ተብሎ
በሚጠራው አካባቢ በየዕለቱ እየሆነ ያለው ሃቅ ግን እጅግ ሰላማዊ ዜጎች በአገራቸውና በምድራቸው በማንም ወንበዴ በማንአለብኝነት
መቀጥቀጥ እና መገድል ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል። በተለይም በአለፉት ሁለት ዓመታት ተባብሶ ቀጥሏል። ይህ የሆነው ግን
በወንጀለኞች እብሪትና ማንአለብኝነት ብቻ ሳይሆን በራሱ ከላይ እስከታች ባለው በመንግሥት አካል ንዝህላልነት፤ አቅመቢስነት ወይም
ግልፅ ድጋፍ ነው። ይህ እየሆነ ያለው በራሱ በአሁኑ ገዥ ፓርቲ በተረቀቀውና በጸደቀው አሁንም በመቃብሬ ላይ ካልሆነ በቀር አይቀየርም
ብሎ ይዞ በሚመራበት “በሕገ መንግሥቱ” ሽፋን ነው። በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በኢትዮጵያ የፈጠራ ትርክት የወለደው ጠማማ አስተሳሰብ
በግለሰቦች አዕምሮ ወስጥ ሰርፆ እና “በሕገ መንግሥት“ ተደግፎ እየተተገበረ በየጊዜው የብዙ ንጹሃን ዜጎች ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ማለፍ
እንደ ተራ ነገር የሚታይ ሆኗል። መንግስት ወንጀል አለመከላከል ብቻ ሳይሆን ወንጀሎች ከተፈጸሙ በኋላም ወንጀለኞችን ለፍርድ
አያቀርብም። ስልጣን ላይ ያለው አካል 27 ዓመታት ስልጣን ላይ ቆይቶ ወንጀሎች ሲፈጽም ነበር። አሁንም አመራሬን ለውጫለሁ ብሎ
ከሁለት ዓመት በላይ ሆኖት የዜጎችን ህይወት ሊታደግ አልቻለም። በዚህም መንግሥትን ፈጽመን እናወግዛለን። ይባስ ብሎ በአሁኑ ወቅት
ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ የሰውን ህይወት የሚቀጥፉትን ወንጀለኞችን ሳያስቆም በቀጣይም የቀሪ ወገኖቻችን ህይወት ዋስትና ሳይሰጥ
በፍጹም ሰላማዊ መንገድ በራሱ በአገዛዙ ሕግ በሚፈቅደው መሰመር የሕዝብ ድምጽ ለመሆን የሚሰሩትን የፖለቲካ አመራሮች በጨለማ
ቤት ያስራል፣ ይደበድባል እንዲሁም ምግብ እንዳያገኙ ይከለክላል። ይህም እጅግ በጣም ዘግናኝ ግፍ ነው። ይህንንም በጸኑ እናውግዛለን።
በመሆኑም፤
፩. አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት እስከ አሁኗ ሰዓት በተግባር እንዳሳየው የዜጎችን ህይወት መታደግ ስላልቻለ ማኅበረሰቡ እራሱን
ከጥቃት እንዲከላከል እናሳሰባለን። መንግስትም ሕዝብን ማትረፍ ባይችል እንኳን ንፁሃን ዜጎች እራሳቸውን ለመከላከል የሚያደርጉትን
ጥረት እንዳያደናቅፍ እንጠይቃለን።
፪. የዓለማቀፉ ማኅበረሰብ በአሁኑ ወቅት “ነፍጠኛ” የሚል ስም በመስጠት በንጹሃን አማሮች እና ጉራጌዎች እንዲሁም ሌሎች ኦሮሞ
ባልሆኑ ማህበረሰቦች ላይ ኦሮሚያ በሚባለው ክልል ወስጥ በግልጽ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመ ሰለሆነና መንግስትም የማስቆም
አቅም እንደሌለው ስለተረጋገጠ የዜጎችን ነፍስ በአስቸኳይ እንዲታደግ ጥሪ እናቀርባለን።
፫.ትህነግን እና የኦሮሞ ጽንፈኞችን ጨምሮ ሁሉንም ወንጀለኞች ለፍርድ የማቅረብ የመንግሥት ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታውም
መሆኑን እያሳሰብን ነገር ግን የድምጽ አልባዎች ድምጽ የሆኑትንና ከወንጀሉ ጋር በምንም መልኩ ግንኙነት የሌላቸውን ሰላማዊ የፖለቲካ
ትግል አራማጆች ማለትም እስክንድር ነጋን፣ ይልቃል ጌትነትን፣ ስንታያሁ ቸኮልን፣ አስቴር ስዩምን እና ሌሎችን ከድርጊቱ ጋር ምንም ግኑኝነት
ሳይኖራቸው የታሰሩ አመራሮችን መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በነፃ በአስችኳይ እንዲፈታ እንጠይቃለን።

፬ እራሱን የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ የሚንቀሳቀሰው ቡድን ሰንደቅ አላማ በመሆን ይታወቅ የነበረው ነገር ግን ከ1985 ዓም ጀምሮ
በበደኖ፣ በአርባጉጉ እንዲሁም በሃረርና በሌሎችም ቦታዎች አማራዎች እና ሌሎች ማሕበረሰቦችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ ገዳዮች ይዘውት
የሚወጡት ሰንደቅ አላማ አሁንም ከግድያ እስከ በህይወት ማቃጠል እንዲሁም የተለያዩ ኢሰብዐዊ ድርጊቶች ጋር የተያያዘው ምልክት
ወይም ሰንደቅ አላማ በሕግ የአሸባሪ ምልክት ተብሎ እንዲታገድ በአፅንኦት እንጠይቃለን!
የዐማራ ባለሙያዎች ማህበር( ዐምባ)
ዋሽንግተን ዲሲ አሜሪካ
ሰኔ 29 ቀን 2012 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *