ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ለኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ የቀረበ ታሪካዊ አገራዊ ጥሪ!

በአዲስ ማኅበራዊ ውል የምንደራደርበትና የኢፌዴሪ ሕገ መንግስትን የማሻሻያው ጊዜ አሁን ነው!
ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ለኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ የቀረበ ታሪካዊ አገራዊ ጥሪ!
***
• ለኢፌዴሪ ጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድ
• ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ
• ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
• ለኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት
• ለመላው የአማራ ሕዝብ
• ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች
• ለተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች
• ለዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ሚዲያዎች
• በአዲስ አበባ ለሚገኙ ለኢትዮጵያ ወዳጅ አገራት ኢምባሲዎች፣ ሚሲዮኖችና ዓለም አቀፍ ተቋማት
ክቡራትና ክቡራን፣

በመላው ዓለም የተከሰተውን የሳምባ ቆልፍ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ተከትሎ በኢትዮጵያም አገራዊ የጤናና የማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ችግር መሆኑን በመገንዘብ በመጪው ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ይካሄዳል ተብሎ ታስቦ የነበረው 6ኛ ዙር አገራዊ ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ማካሄድ እንደማይችልና ምርጫውም ላልተወሰነ ጊዜ እንደተራዘመ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በዚህ አመት መጨረሻ የስልጣን ዘመኑ የሚጠናቀቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምን ሊደረግ እንደሚችል በሁላችንም ዘንድ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል፡፡

በኢፌዴሪ ሕገ መንግስትም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ ሕጎች ምርጫ ስለማራዘምም ሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የአስፈጻሚውን ስልጣን ማራዘም የሚቻልበት ግልጽ ድንጋጌ የለም፡፡ ስለዚህ ሁኔታው የብሔራዊ የአንድነትና ጊዜያዊ መንግስት የማቋቋም፤ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት አዲስ ማኅበራዊ ውል የምንገባበትን ጊዜ አስፈላጊ እንዳደረገው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በጥብቅ ያምናል፡፡ ስለዚህ የኢፌደሪ መንግስት ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የሕገ-መንግስት ማሻሻያ ሂደት እንዲያስጀምር አብን ብሔራዊ ጥሪ እያቀረበ መላው የአማራ ሕዝብና ኢትዮጵያዊያን የአብንን ብሔራዊ ጥሪ ደግፋችሁ ለብሔራዊ የአንድነትና የጊዜያዊ መንግስት መቋቋም መሳካትና ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ይሁንታ የሰጡትና ዘብ የሚቆሙለት የተሻሻለ ወይም አዲስ ሕገ-መንግስት እንዲዘጋጅ ለጀመርነው ትግል ከጎናችን እንድትቆሙ ታሪካዊ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ አብን አሁን በስራ ላይ ካለው የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት ዉስጥ የሚከተሉት 15 አንቀጾች በማሻሻያው እንዲካተቱ በመላው ኢትዮጵያዊያንና በአማራ ሕዝብ ስም ለመንግስት ይፋዊ ጥሪዉን ማስተላለፍ ይወዳል፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መሻሻልና መቀየር ያለባቸው የሕገ መንግስቱ አንቀጽ ናቸው ብሎ ያስጠናቸውና የለያቸው የሚከተሉት ናቸው፡፡

መግቢያ:- «እኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች» የሚለው መግቢያውና ስያሜው ገጽ ላይ ያለው ጥርት ያለ ትርጉም የሌለው በሶሻሊስታዊ እሳቤ የተቃኘ አገላለጽ አገራዊ አንድነትን ሊገልጽ፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን ሊያጎላ በሚችል «የኢትዮጵያ ሕዝብ» በሚል አገላለጽ መተካት አለበት። በቋንቋና ኃይማኖት የተለያዩ ሕዝቦች ያሏቸው አገራት ሳይቀሩ የሕገ-መንግስታቸውን መግቢያ «እኛ የዚህ አገር ሕዝቦች..» ብለው ይጀምራሉ። ለምሳሌ የደቡብ አፍሪቃና አሜሪካ ሕገ መንግስቶችን ማየት ይቻላል።

አንቀጽ 3:- የኢትዮጵያ ሰንደቀላማ ላይ ምንም አይነት አርማ ሊቀመጥበት አይገባም። ይህ ከአባቶቻችን የወረስነው፣ ለልጆቻችን የምናወርሰው፣ አባቶቻችን የሞቱለትና እኛም የምንሞትለት ሰንደቅ አላማ ምልዑ የሆነ ነው። የሕዝቦችን ተስፋ ለማመልከት ቢጫውን ቀለም፥ የኢትዮጵያን ሕዝብና የኃይማኖቶችን እኩልነት ለማመልከት የሶስቱ ቀለማት እኩልነትን መጠቀም ይቻላል።

አንቀጽ 5፡- አማርኛ የፌደራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ መሆን መቻል አለበት። አማርኛ ቋንቋ ኢትዮጵያን ካስተሳሰሩ ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ክር ነው። ስለዚህ አማርኛ ቋንቋ የፌደራል መንግስቱ ስራ ለመስራት ወይም አገልግሎት ለመስጠት የሚጠቀምበት ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሕዝብ ሁኖ ሁሉም ክልሎች የሚያሳድጉት፣ የሚያጎለብቱት፣ የሚጠቀሙበት ብሔራዊ ቋንቋ መሆን አለበት። አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ ባለመሆኑ የተነሳና የፌደራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ ብቻ በሚል በመጠቀሱ የተነሳ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ ተፅዕኖ እያደረሰባቸው ይገኛል፤ በዚህም በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ አማራዎችም ቋንቋቸውን እንዳይጠቀሙ እየተደረገ ነው። ለዚህ ምሳሌ በኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ የንግድ ታፔላዎች ላይ የሚደርሱ ማቅለሞች እና ማፍረሶች አስረጂዎች ናቸው።

አንቀጽ 8፡- ላይ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። አንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ መኖሩን ያመላክታል። ይህ ማዕከላዊነትን ወይንም ወደ አንድ መጨፍለቅን አያሳይም፡፡ አለበለዚያ ጉዳዩ የፌደሬሽን ሳይሆን የኮንፌደሬሽን ይሆናል ማለት ነው፡፡

አንቀጽ 39:- መገንጠል መሠረታዊ የሆነው የፌደራሊዝም ጽንሰ ኃሳብ ማለትም የድርድር ጉዳይን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ተግዳሮት ነው፡፡ መገንጠል ከፌደራሊዝም ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፤ መገንጠል ያልሰለጠነ ድርድርን ይጋርጣል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሊሰጠው ይገባል፤ ነገር ግን የመገንጠል መብት ሊሰጠው አይገባም። ይህ የመገንጠል ጽንሰ ኃሳብ ያለምንም ሁኔታዎች (Conditions) በሕገ መንግስት ማዕቀፍ ውስጥ ማካተት የአገሪቱን ሉዓላዊ አንድነት ለአደጋ ማጋለጥ ነው።

ከአንቀጽ 45 በኋላ ስላሉ አንቀጾች፡- አገሪቱ የፌደራል መንግስት አወቃቀር ልትከተል ትችላለች። ነገር ግን ክልሎች ሲዋቀሩ አንድን ክልል ለአንድ ብሔር የመስጠት አካሄድን ሊያስቀር በሚችልና በክልሎች መካከል የሕዝብ ብዛትና የእድገት ልዩነትን በአመጣጠነ መልኩ ታሪክንና መልከዓምድራዊ አቀማመጥን፣ የሕዝብ አሰፋፈርንና ቋንቋን ወዘተ. መስፈርቶች ባማከለ መጠን ለአገሪቱ አንድነትና ለሕዝብ ሰላማዊ መስተጋብር መሠረት በሚጥል መልኩ መሆን አለበት።

በአንቀጽ 47 መሠረት የተቋቋሙ ክልሎች መፍረስ አለባቸው። አሁን ያለው የክልሎች አወቃቀር የአማራን ሕዝብ ታሪካዊ ግዛቶች የከፋፈለና የአማራን ሕዝብ የማንነት፣ የቋንቋ፣ የባኅል፣ የሕይዎት፣ የኢኮኖሚ ወዘተ. መብቶች የማያስከብር ነው። ለምሳሌ ከላይ በጠቅላላው ክፍል በተጠቀሰው መልኩ መተከል የሚባለው የቤንሻንጉል ክልል ግዛት አማራ የሚበዛበት በታሪክም የአማራ ሕዝብ መኖሪያ የሆነ ቀየ የፌደራሉ ሕገ መንግስት እውቅና ለሰጠው የቤንሻንጉል ክልል ተሰጥቷል። ይህ የቤንሻንጉል ክልል ደግሞ በሕገ መንግስት የአማራን ሕዝብ የክልሉ ባለቤት አይደለም ብሎ ደንግጓል። በዚህ መሠረት ቤንሻንጉል ክልል ውስጥ የሚኖር የአማራ ሕዝብ አገር እና ዕርስት አልባ ነው ማለት ነው። ይህ አካሄድ ሌሎች ክልሎች ውስጥም አለ። ለምሳሌ፦ የሃረሪ ክልል ባለቤት የሃደሬ ሕዝብ ነው። ነገር ግን አማራ በክልሉ ውስጥ በቁጥር ይልቃል። ይህ በቁጥር የሚልቅ ሕዝብ ምንም አይነት የባለቤትነት መብት የለውም ወይም ከሕዝቡ በኋላ በመጣ የፌደራልና የክልል ሕገ መንግስቶችና ሕጎች የተነሳ አገር እና መብት አልባ ሁኗል። ይህ የክልል ባለቤትነትን ለአንድ ወይም ለተወሰነ ቡድን መስጠትና የአማራን ሕዝብ አገር አልባ ማድረግ በክልሎች ውስጥ በኢኮኖሚም ሆነ በፓለቲካው እንዲገፋ የሚያደርግ አካሄድ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *