ከዐማራ ድርጅቶችና ማኅበራት ስብስብ (ዐድማስ) በአማራ ወገናችንና በሌሎች ወንድሞቹ ላይ ስለሚፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል የተሰጠ መግለጫ

ከዐማራ ድርጅቶችና ማኅበራት ስብስብ (ዐድማስ) በአማራ ወገናችንና በሌሎች ወንድሞቹ ላይ ስለሚፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል የተሰጠ መግለጫ
በኢትዮጵያ በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውና ግማሽ ምዕተ ዓመትን የተሻገረው ጥቃት መልኩን እየቀያየረ ተባብሶ ቀጥሏል። በደደቢት ተጸንሶና በሰንዓፈ ተወልዶ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ሀገራችንን በቋንቋ በከፋፈላትና በ”ሕገ መንግሥት” ስም በተሰየመው ሰነድ የተመሰረተው ፌደራሊዝም የአማራን ሕዝብ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ሕይወት ባይተዋር በማድረግ፤ ተፈጥሮአዊ ዕድገቱ ወደሆነው የአማራን ሕዝብ ዘር ወደማጥፋት አረመኔያዊ ድርጊት ተሸጋግሯል።
መላው ዓለም እንደሚያስታውሰው፤ ከጥቂት ወራት በፊት በኦሮሞ ክልል የሚንቀሳቀስ አንድ ፅንፈኛ ፖለቲከኛ መንግስት ያቆመልኝን ጠባቂዎች ሊያነሳብኝ ነው በሚል ትንሽ ሰበብ በፅንፈኛ ተከታዮቹ ቢያንስ 86 የአማራ ተወላጆችና የአማራ ተወላጅ የመሰሏቸውን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ አሰቃይተው የገደሉና በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ዜጎችን ደም አፍስሰው እስካሁን የተጠየቀ ስለመኖሩ በይፋ አይታወቅም። አሁንም ያለፈው አልበቃ ያላቸው ይመስል በአማራ ሕዝብ ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ለመፈፀም ሰበብ ለማበጀት ብዙ ርቀት ተጓዙ። ድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ በፅንፈኛ ሚዲያቸው የፈለገውን ሁሉ እንዲናገርና በማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ እንዲሆን ካመቻቹ በኋላ እንዲገደል አድርገዋል። ይህንንም ተከትሎ በአማራ ተወላጆች ላይ ያቀዱትን የዘር ማጥፋት ወንጀል ባደራጇቸው ጀሌዎች አማካኝነት ተገበሩ። በዚህም በኦሮሞ ክልል ብቻ መንግስት ባመነው የጸጥታ አስከባሪዎችን ጨምሮ ፪፻፴፮ (ሁለት መቶ ሰላሳ ስድስት) ሰዎች በአሰቃቂ ግድያ ሕይወታቸውን እንዳጡ የተነገረ ሲሆን፤ ከዚህ በብዙ እጥፍ ሊቆጠሩ የሚችሉ ንጹሓን የአማራ ተወላጆችና ጠላት ብለው የቆጠሩት ዕምነት ተከታዮች ሊሞቱ እንደሚችሉ ይገመታል። በብዙ እጥፍ የሚልቁ ሌሎች የአማራ ተወላጆችና ሌሎች ዜጎችም የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ይገመታል። በተጨማሪም፤ በብዙ ሚልየኖች ብር የሚገመት የንጹሓን የዕድሜ ልክ የላብ ውጤት የሆነ ንብረት እንደወደመ ይገመታል።
ይህ ሁሉ እየተፈፀመ ያለው በኦሮሞ ክልልና በፅንፈኞቻቸው ሆኖ ሳለ “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” እንዲሉ ወደ እስር ቤት እየተጋዙና እየተንገላቱ የሚገኙት በተለያየ አጋጣሚ ለአማራ ሕዝብ መብትና ጥቅም እንዲሁም ለአገር አንድነትና ዲሞክራሲ የታገሉ የፖለቲካ መሪዎች ናቸው። ለመሆኑ፤ የእስክንድር ነጋ፣ የእንጅነር ይልቃል ጌትነት፣ የአስቴር (ቀለብ) ሥዩም፣ የልደቱ አያሌውና የሌሎችም እስር በፅንፈኞች ታቅዶ ከተተገበረው የዘር ማጥፋት ወንጀል ጋር ምን ሊያያይዘው ቻለ? መልሱን የሚያውቁት አሳሪዎቹ ብቻ ናቸው። የአሥራት ሚዲያን መወንጀልና መመርመርስ የዘር ማጥፋት ከሚታወጅባቸው OMN እና DW ጋር ምን አቆራኘው? የሁሉም መልስ የሚያመራው አማራ ከዜግነት ተራ ወርዶ እንዲታይ ወዳደረገው የትህነግ ሕገ-አራዊት፣ በትህነግና በኦነግ ትርክት ወደተወናበዱ ካድሬዎችና የፖለቲካ አመራሮች እንዲሁም በዚህ ጸረ-አማራ ትርክት ወደተጠለፉ የፍትሕና የጸጥታ ተቋማት እንደሆነ እናምናለን።
በመሆኑም ዐድማስ፤
፩ኛ) መንግስት በኦሮሞ ክልል የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆችንና የሌሎች ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያንን በአገሪቱ ተዘዋውሮ በሰላም የመኖር፣ የመስራትና ንብረት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብት ያስከብር ዘንድ፤
፪ኛ) በመንግስት አሰራር ያልተደሰተ ማንኛውም አካል ችግሩን ከመንግስት አካላት ጋር በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር መፍታት ካለዚያም ተቃውሞውን ማሰማት ሲገባው በሰላማዊ ህዝብ ላይ ግድያ፣ የአካል ጉዳት ማድረስና ንብረት ማውደም በአስቸኳይ ያቆም ዘንድ፤
፫ኛ) ይህንን ተላልፎ በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ አደጋ ለሚጥል ለማንኛውም ኃይል ሕግ የማስከበር ኃላፊነት ያለበት አካል ሲቻል ሳይደርስ ይከላከል ዘንድ፤ ካለበለዚያ አጥፊዎችን ለፍርድ ያቀርብ ዘንድ፤
፬ኛ) ጥቃት ለደረሰባቸውና ከመቅጽበት ቤትና ንብረት አልባ የሆኑ ዜጎችን ከጊዜያዊ ችግሮቻቸው የሚላቀቁበትን መንግሥት ያመቻች ዘንድ፣ ለዘላቂው ተገቢና ተመጣጣኝ ካሳ ተከፍሎአቸው ወደአምራች ተግባራቸው በቶሎ እንዲሸጋገሩ ያደርግ ዘንድ እንዲሁም በግፍ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ዘላለማዊ መታሰቢያ ያቆምላቸው ዘንድ፤
፭ኛ) መንግሥት በኦሮሚያ ክልል በጥቅምትና በሰኔ ፳፻፲፪ ዓ.ም. የተካሄዱትን የዘር ማጥፋት ወንጀሎች በነጻና በገለልተኛ አካላት አስመርምሮ ጥፋተኞችን ለፍርድ ያቀርብ ዘንድ፤ ተበዳዮችንም ተመጣጣኝ ካሳ ይክስ ዘንድ፤
፮ኛ) መንግሥት በገለልተኛ ምርመራ ውጤት በመመርኮዝ ሰላም የማስጠበቅና ሕግ የማስከበር ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ እንዲሁም አውቀውና ፈቅደው እነዚህ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ ባስቻሉ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ተገቢውን የአስተዳደርና የሕግ ዕርምጃ ይወስድ ዘንድ፤
፯ኛ) መንግሥት በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በመሆን የዘር ማጥፋት ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የነበሩ ግለሰቦችን፣ ቡድኖችንና የብዙኃን መገናኛዎችን ከሕግ ፊት ያቀርብ ዘንድ፤
፰ኛ) ጩኸታቸውን ተነጥቀው በእስር እየተንገላቱ ያሉ ንጹሓን ዜጎችና የፖለቲካ መሪዎች በአስቸኳይ በነጻ ይለቀቁ ዘንድ እንጠይቃለን።
በተጨማሪም፤ በሁሉም የዓለም ማዕዘናት የምትኖሩ የአማራ ተወላጆች፣ እንዲሁም ሰላምና አንድነትን ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፤ ይህ ወቅት ፅንፈኛው፣ አክራሪውና አልጠግብ ባዩ ኃይል ህዝባችንን ብሎም አያት ቅድመ-አያቶቻችን በደምና በአጥንታቸው አስከብረው ያቆዩልንን ሀገራችንን ለከፋ አደጋ ከመዳረጉ በፊት፣ ወገናችንንም ለከፋ አደጋ ከመዳረጉ በፊት በጋራ መቆም እንደሚገባን ዐድማስ ይገነዘባል። ስለሆነም፤
፩ኛ) ከአገር ውጪ የምንኖር የአማራ ተወላጆችና ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ሀገር የምትኖረው ህዝብ በነፃነት ሲኖር ነውና ለምንኖርበት ሀገርና የአካባቢ ተመራጭ ባለስልጣን ሁሉ በሀገራችን በኦሮሞ ክልል በሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆችና በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ እየተደረገ ያለውንና የታቀደውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በተደራጀ፣ በተቀናጀና በተናበበ መልኩ ለማስረዳት ጠንክረን እንሰራ ዘንድ፤
፪ኛ) የአማራን ህዝብ ለማጥቃት ሴራ ጠንስሰው ጥቃቱንም በብዙ ሺህ የአማራ ተወላጅ ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ፈፅመው ሳለ መንግስት ለኢትዮጵያ አንድነትና ለዜጎቿ ወንድማማችነት የሚታገሉትንና ራሳቸውን ለመከላከል በሞከሩ የአማራ ተወላጆች ላይ እየፈፀመ የሚገኘውን እስርና እንግልት በአስቸኳይ እናስቆም ዘንድ፤
፫ኛ) በደረሰባቸው ኢሰብዓዊ ጥቃት ለተጎዱ ወገኖቻችን በተቻለን አቅም ድጋፍ እናደርግ ዘንድ እንጠይቃለን።
የዐማራ ድርጅቶችና ማኅበራት ስብሰብ (ዐድማስ)፤
ሐምሌ ፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓመተ ምህረት።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *