ከጠቃላይ ዐቃቤ ሕግና ከፌዴራል ፖሊስ በአሥራት ሚድያ ላይ የቀረበውን ሐሰተኛ ውንጀላ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

ከጠቃላይ ዐቃቤ ሕግና ከፌዴራል ፖሊስ በአሥራት ሚድያ ላይ የቀረበውን ሐሰተኛ ውንጀላ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ፤
ከሁሉ አስቀድመን በሀገራችን ውስጥ ግለሰቦችን በመግደል የፖለቲካ የበላይነትን ለመቆጣጠር የሚሞክሩ ኃይሎች ከሀገር ግንባታ በተቃራኒ የቆሙና የአፍራሽነት ሚናቸው ከፍተኛ የሆነ በመሆኑ፤ ትናንት በሌሎች ዛሬ ደግሞ በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈጸመውን ግድያ የአሥራት ሚድያ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ በጽኑ የሚያወግዘው መሆኑን እያሳወቅን፤ ለአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ቤተሰቦች፣ ዘመድ-ወዳጆችና አድናቂዎች መጽናናትን እንመኛለን።
በተጨማሪም፤ በኢትዮጵያ የሴራ ፖለቲካ ቀርቶ፤ በአሉበት አካባቢ ፖለቲካ እንኳ ምንም ዓይነት ድርሻ የሌላቸው ንጹሐን ዜጎች በማንነታቸው ብቻ ተለይተው የሚደረግባቸውን አካላዊ፣ ስነ-አዕምሮአዊና ማኅበራዊ ጥቃት እናወግዛለን። ከዚህም ተያይዞ በደረሰው የሕይወትና የንብረት ጥፋት የተሰማንን ከፍተኛ ሐዘን እየገለጽን፤ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች መጽናናትን እንመኛለን። የሚመለከታቸው የፍትሕ እና የጸጥታ አካላትም ለዚህ ዙር ጥፋት ተጠያቂዎችን ለፍርድ እንዲያቀርቡ፣ ካሁን በፊት በደረሱ ተመሳሳይ ጥቃቶች ተሳታፊ በነበሩ አካላት ላይ የተወሰዱ ሕጋዊ ዕርምጃዎችን ይፋ እንዲያደርጉ፤ እንዲሁም ለወደፊት ተመሳሳይ ጥቃቶች እንዳይካሄዱ አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ እንዲደያደርጉ እንጠይቃለን።
አሥራት ሚድያ፤ ለአማራ ሕዝብና ድምጽ ለሌላቸው ኢትዮጵያውያን በመላ ድምፅ እንዲሆን በአማራ ልጆችና የአማራ ወዳጆች የተቋቋመና በአየር ላይ ከዋለበት ጀምሮ፤ በአጠቃላይ ለሀገር ግንባታ ትርጉም ያላቸው ሃሳቦች፤ እንዲሁም ለተገፉ ወገኖች አማራጭ ድምጽ በመሆን ሲያገለግል ቆይቷል።
አሥራት ሚድያ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ፤ የሙያ ሥነ-ምግባርና የሀገራችንን ሕግ በማክበር፤ ለሀገር አንድነት፣ ለሕዝብ ሰላም፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ለዜጎች ፍትሕና ዕኩልነት መሠረታዊ መርኆዎች ላይ በመቆም ኃላፊነቱን ሲወጣ ቆይቷል። ከነዚህ መሠረታዊ መርኆዎች በተጻራሪ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ላይ እያሳረፉት ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ በማጋለጥ፤ ሕዝብና መንግሥት እንዲያወቁት በማድረግ ሰፊ ሥራ መሥራቱ ይታወቃል። አሥራት ሚድያ ከብሮድካስት ባለሥልጣን የኮረስፖንደንት አገልግሎት ፈቃድ ወስዶ እየሰራ ያለ በመሆኑ፤ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለሚድያዎች የሚሰጠው የክትትልና ግምገማ (ሚድያ ሞኒተሪንግ)፤ በሰራናቸው ዜናዎችና ፕሮግራሞች ላይ አስተያየትና ጥቆማ በመስጠት ላይ የተመሰረተ በጎ ግንኙነት አለን።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሀገራችን ካላት የሚድያ ዐዋጅ አንጻር፤ መሰረታችንን ሀገር ውስጥ አድርገን በተሟላ መልኩ እንድንሰራ በውይይትና በደብዳቤ አሳውቆናል። የአሥራት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድም ጉዳዩን በአዎንታዊ መልክ ተቀብሎ እየመከረበት ይገኛል። ዕውነታው ይህ ሆኖ እያለ፤ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ፌዴራል ፖሊስ በሰጧቸው መግለጫዎች ላይ፤ ሀገር እንዲፈርስ፣ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ እንዲነሳ ቅስቀሳና የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ሰርተዋል ከተባሉ ሚድያዎች ጋር አሥራት ሚድያም ተካትቶ ቀርቧል። ነገር ግን፤
፩ኛ) የአሥራት ሚድያ የሳተላይት ስርጭት ከክፍያና ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ፤ ክስተቱ ከመፈጸሙ በፊት ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. (24 June 2020) ከቀኑ ከ8፡00 ሰዓት ጀምሮ ስርጭቱ በአየር ላይ ያልነበረ መሆኑ፤
፪ኛ) የሥርጭቱን መቋረጥ አስመልክቶ የአሥራት ሚድያ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ለአድማጭ-ተመልካቾች በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ ስለስርጭቱ መቋረጥ ያሳወቀ መሆኑ፤
፫ኛ) ከዚህ በፊት አሥራት ሚድያ በሠራቸው ዜናዎችና ፕሮግራሞች ላይ ከሙያዊ መርኆዎችና ከሀገራችን ብሔራዊ ጥቅሞች ተጻራሪ ቆሞ የማያውቅ መሆኑ፤ ይህም የአሥራት መሠረታዊ ዓላማ በመሆኑ፤
፬ኛ) ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ጋር የምንሰራቸውን ዜናዎችና ፕሮግራሞች በተመለከተ አዎንታዊ የሆነ የድጋፍና የክትትል ግንኙነት ያለን መሆኑ ይታወቃል።
በመሬት ላይ ያለው ሐቅ ከላይ የተገለጸው ሆኖ እያለ፤
፩ኛ) የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፌዴራል ፖሊስ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ብዙኃን መገናኛ ተቋማት በሰጡት መግለጫና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት አሥራት ሚድያን አፍራሽና የጦርነት ዕወጃ እንዳደረገ፤ የዘር ጭፍጨፋ እንዲደረግ ቅስቀሳ እንዳካሄደ ተደርጎ የቀረበበት ዐውድ ፍጹም ውሸት የሆነና የሕዝቡን ሞራል ያልጠበቀ ሐሰተኛ ሪፖርት ሆኖ አግኝተነዋል። በመሆኑም በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና በፌዴራል ፖሊስ በሚድያው ላይ ለተፈጸመው ሐሰተኛ ፍረጃና ስም ማጥፋት፤ ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ይቅርታና ማስተባበያ እንዲሰጥ እንጠይቃለን።
፪ኛ) አሥራት ሚድያ በታማኝነት እያገለገለ ላለው ሕዝብ ሐሰተኛ ሪፖርት በማቅረብ የፍትሕ ተቋማቱ በፈጸሙት የሞራል ጉዳት ሕዝባችንን በይፋ እንዲጠይቁ እናሳስባለን።
፫ኛ) ሕዝቡ ለለውጥ ከታገለላቸው የዲሞክራሲያዊ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት መሆኑ ይታወቃል። በዚህ መሠረት መንግሥት ለሚድያዎች በሰጠው ልዩ ትኩረት እስከ ክፍለ አህጉራዊ የሚዘልቅ መዋቅር ዘርግተው እንዲሰሩ እገዛ እየተደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ የሚድያን ሚና የሚያቀጭጭና የሃሳብ ነጻነትን የሚጋፋ ሐሰተኛ ውንጀላ መንጸባረቁ ሕዝብ ታግሎ የጣለውን የአፈና ሥርዓት እንድናስታውስ አድርጎናል። የሆነ ሆኖ፤ ለወደፊትም አሥራት ሚድያ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ፣ ሕግን አክብሮ፣ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም አስቀድሞ፣ የሕዝብን ሰላምና አንድነት አገናዝቦ፣ ሙያዊ ኃላፊነትን እየተወጣ የሚቀጥል መሆኑን ለማረጋገጥ እንወዳለን።
ድር ቢያብር፤ አንበሳ ያስር!
የአሥራት ሚድያ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ፤
ሰኔ ፳፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓመተ ምህረት።