ግልፅ ደብዳቤ በሐረር ከተማ እና በከተማው ዙሪያ ለምትኖሩ የዘመኑ ባለስልጣናት

የተወደዳችሁ የሐረር ከተማ እና አካባቢዉ የወቅቱ ገዢዎች፦

የልዑል ራስ መኮንንን ሃዉልት ማስፈረስ ስለቻላችሁ ተደሰታችሁ ይሆን? የዚህን አሳፋሪ እብደት ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ እንደምታ በመጠኑም ቢሆን ትረዳላችሁ ብዬ ስለምገምት ተደስታችኋል ብዬ አላስብም፡፡ ሆኖም አብዛኞቻችሁ የህወሓት/ኢህአዴግ ትዉልድ እና የዉሸት ትርክት ዉጤት ስለሆናችሁ የዚህ ጋጠወጥነት አካል ልትሆኑ እንደምትችሉም እገምታለሁ፡፡

የልዑል ራስ መኮንንን ሃዉልት ማፍረስ የአደሬም ሆነ የሐረር ኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት እንዳልሆነ ሁላችንም እናዉቃለን!! ሃሳቡን ያመነጨው ሰኔ ፩፱፻፹፫  ዓም ደንገጎ ላይ በደረሰበት ዉርደት ምክንያት ክርስቲያኑን እና አማራ የሚለዉን ሕዝብ ጠላት ያደረገው የትግራዩን ወንበዴ እየመራ የመጣው የሳሞራ የኑስ መንጋ እንደሆነ ቋሚ ምስክር ነን፡፡ ከልዑል ራስ መኮንን ልፋት እና ድካም ይልቅ ሲያዋርዳችሁ ለኖረው እና ከሰዉነት አዉርዶ ጎሳ አጥር ዉስጥ ለከተታችሁ ወንበዴ ቃል መታመናችሁ ሊያሳፍራችሁ እንጅ ሊያኮራችሁ አይገባም!!

የአደሬ እና የኦሮሞ ሽማግሌዎችን ብትጠይቁ ስለ ልዑል ራስ መኮንን የሚከተለዉን ትሰማላችሁ፡

 

፩. የዳግማዊ ምኒሊክ ሰራዊት ሐረርን ከመቆጣጠሩ አንድ እና ሁለት ዓመት በፊት አሚር አብዱላሂ  በክርስቲያኖች እና በዉጭ አገር ሰዎች ላይ ይህ ነው የማይባል ግፍ እና መከራ ሲያደርስ ነበር፡፡ ክርስቲያኖችን እስላም ካልሆናችሁ በማለት እና አዉሮፓዉያንን በጭፍን በመጥላት ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረው አሚር የንግድ ስራን እጅግ ከባድ አድርጎት ነበር፡፡  መገበያያ ገንዘብ ሳይቀር እቀይራለሁ ብሎ ቆርቆር ቀጥቅጦ ገንዘብ ነው ሲል በአካባቢው ይኖር የነበረው የኢቱ እና የሶማሌ ጎሳ ሌላ ገበያ በመሄዱ ምክንያት ሰው ምን ያህል እንደተሰቃዬ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ስቃይ ያበቃው ዳግማዊ ምኒልክ ሐረር ከደረሱ እና ራስ መኮንን የሐረር ገዢ ከሆኑ በኋላ ነው፡፡

 

፪. አሁን የአደሬ ባህላዊ ልብስ ተብሎ የሚለበሰው በሃር ያጌጠ ሱሪ እና ቀሚስ ወደ ሐረር የመጣው እጅግ ጨካኝ የነበረው አሚር አብዱላሂ የሚመራዉን ጦር በ ፲፭ ደቂቃ በትነው ሐረር የገቡት ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ጥር ፩፰፻፸፱ ዓም ራስ መኮንንን የሐረር ገዢ አድርገው የአሚር አብዱላሂን ዘመድ አሊ አቡበከርን ደግሞ የእስላሙ ማህበረሰብ መሪ አድርገው ከሾሙ በኋላ ነው፡፡ የዛን ጊዜ ሰሜን ሶማልያ ዉስጥ የነበሩ የህንድ ነጋዴዎች ወደ ሐረር መጡ፡፡ የህንድን ልብስም እየያዙ መምጣት ጀመሩ፡፡ በአሚሩ ዘመን ጫማ እንኳን እንዲያደርጉ የማይፈቀድላቸው የአሚሩ ቤተሰብ ያልሆኑ ተራ ዜጎች የሐረ ልብስ መልበስ ጀመሩ፡፡ አሁን ያለዉን ባህላዊ ልብስ ከህንድ ልብስ ጋር ማስተያየቱ ብዙ ያስተምራል፡፡ ይህ የሆነው ራስ መኮንን ሁሉኑም እኩል ስላደረጉት ነው፡፡

 

፫. ጨለንቆ ላይ ከደረሰው ዉርደት ይልቅ የሐረርን ሰው እጅግ ያሳዘነው ተቆርቋሪ መስሎ የህዝቡ አለቃ ሆኖ የተሾመዉ አሊ አቡበከር ጨለንቆ የሞቱትን ሰዎች ንብረት መዉረሱ እና ቤተሰባቸውን መበተኑ ነበር፡፡ “ለግብፅ ትገብሩት የነበረዉን ብቻ ለኔም ገብሩ” የሚለዉን የዳግማዊ ምኒልክ አዋጅ ሽሮ ሰዉን ያለአግባብ ሲዘርፍ የነበረው አሊ አቡበከር ነበር፡፡ ታሪክ አለማወቅ እና የትግራይ ወንበዴዎች ፍራቻ አደነቆሯችሁ እንጂ አሊ አቡበከርን ለማስነሳት ራስ መኮንን ጋር ስንት ሽማግሌ ነው የተላከው?

 

፬.  አሚር አብዱላሂን አስፈልገው፣ አስይዘው፣ ምህረት አድርገው፣ ሾመዉ በከተማዉ ዉስጥ ሲያኖሩት ነበር፡፡ አሚሩ ምንድን ነው ያደረገው? ሰዉንም እሳቸዉንም ሰላም ነስቶ ተዉ ቢባል እምቢ ብሎ አገር ሲያምስ ታሰረ፣ ተፈታ እንደገና ሥራ ተሰጠው፡፡ ኖረና በሰላም ሞተ!!

 

፭. የግብፅ ግብር እጅግ ከባድ እንደነበር እና እንዲቀጥል መደረጉ ሰዉን እጅግ እንዳሰቃየዉ የተመለከቱት ብሎም ዳግማዊ ምኒልክ ፊት ቀርበው ለመጀመሪያ ጊዜ ግብር በዝቷል ብለው በከፍተኛ ደረጃ ያስቀነሱት ልዑል ራስ መኮንን ናቸው፡፡

 

፮. የሐረር ከተማ ሕዝብ በጀጎል ዉስጥ ብቻ ታጥሮ በዙሪያው ባሉ የኢቱ [ዛሬ ኦሮሞ] ጎሳዎች እየተዘረፈ እና አደጋ እየደረሰበት በስጋት ሲኖር ነበር፡፡ የጀጎል ነዋሪ የሰላም አየር የተነፈሰው ራስ መኮንን ሐረር ከመጡ ነው፡፡ ከጀጎልም ዉስጥ ወጥቶ የራሱን ሽንት ቤት እና ግቢ ሰርቶ መኖር የጀመረው ራስ መኮንን ሐረር ከመጡ በኋላ ነው፡፡

 

፯.  የከተማዉ ሰው ከሐረር ወጥቶ ለንግድም ሆነ ለስራ ወደሸዋ መሄድ የጀመረው ራስ መኮንን የሐረር ገዢ ከሆኑ በኋላ ነው፡፡ ከዛ በፊት በዋናነት ሶማሌዎች አፋሮች አረቦች እና አርጎባዎች በተወሰነ መጠን ደግሞ ግብፆች ቱርኮች አርመኖች እና ጣሊያኖች እንጂ አንድም አደሬ ከጀጎል ወጥቶ ለንግድ ወይም ለስራ ብሎ ሸዋ ወይም ታጁራ ወይም ዘይላ እንደ ሄደ የሚያሳይ ታሪክ የለም፡፡

 

፰. የአደሬ ቤተሰብ እርስ በርሱ የመጋባት [ለረጅም ጊዜ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያድረስ የኖረው] ልምድ እየቀረ የመጣው ሌሎች በኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉ ጎሳዎች ወደ ሐረር ሲመጡ እና የአደሬ ጎሳ አባላትም ወደሌላዉ የኢትዮጵያ ክፍል መሄድ እና መቀላቀል ከጀመሩ በኋላ ነው፡፡ ይሄም የጀመረው በራስ መኮንን ዘመን ሲሆን የመጀመሪያዉ ፍልሰት ወደ ድሬዳዋ ነበር፡፡ ጣልያን ከኢትዮጵያ ከተባረር በኋላ ደግሞ ወደ ሸዋ ሰዉ ፈለሰ፣ ሃብታም የነጋዴ ቤተሰቦችም መፈጠር ጀመሩ፡፡ ይሄም የሆነው በንጉሰ ነገስት ሃይለስላሴ ዘመን ነው፡፡ እኚህ ንጉስም የራስ መኮንን ልጅ ናቸው፡፡

 

፱.  በኢትዮጵያ ዉስጥ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ስልክ የገባው ሐረር ከተማ ነው፡፡ መደበኛ ትምህርት ቤት የተከፈተው ሐረር ነው፡፡ የባቡር ሃዲድ የተሰራው ሐረርጌ ነው፡፡ ሌላም በርካታ ሥራ ተሰርቷል፡፡ ይሄ ሁሉ የራስ መኮንን ድካም እና ልፋት ያረፈበት ነው፡፡

 

፲. ራስ መኮንንን ላለፉት ፳፱ አመታት ከምትወቅሱበት ታሪክ አንዱ “መስኪድ አፍርሶ ቤተ ክርስቲያን ሰራ” የሚለው ነው፡፡  ለመሆኑ ብዙ እስላም የሚኖርበትን አሩሲን እና አዉሳን አልፈው የመጡት ዳግማዊ ምኒልክ እና ራስ መኮንን ለምን ሐረር ሲደርሱ መስኪድ አፈረሱ? የአሚር አብዱላሂ ሚና ምንድን ነው? ሐረር ከተማ ሲገቡ ስንት መስኪድ ነበር? ራስ መኮንን ያፈረሱት መስኪድ ማን ይባላል? ለምን እሱን ለይተው አፈረሱ? ራስ መኮንን ሌላ መስኪድ እንዳያፈርሱ ሊያቆማቸው የሚችል ኃይል በዛን ወቅት ነበር? ለምን ቤተ ክርስቲያን ሰሩ? የሚሉትን ጥያቄዎች በእዉነት መልሱና እዉነቱን ተናገሩ፡፡ ግብፆች የሰሩትና ገና አስር ዓመት ያልሞላው መስኪድ የፈረሰው በአሚር አብዱላሂ ጋጠ ወጥነት ምክንያት ነው፡፡ ገና የ፲፭ ደቂቃው ጦርነት ጨለንቆ ላይ ሳይደረግ ሂርና ሆነው እና ሐረርም ድል አድርገው ከገቡ በኋላ በሰላም እንዲገባ እና እንዲገብር ሲላክበት አሚር አብዱላሂ ምን ብሎ ነው የመለሰው? የአሚሩ መልስ በዘመኑ ከነበረው አመለካከት አኳያ ምን እንዲያስከትል ነበር የሚጠበቀው? ልክ ነው እድሜ ለዘመኑ የወረደ ጎሰኝነት እና አክራሪነት ራስ መኮንን ባዕድ አሚር አብዱላሂ ደግሞ ወገን ነው፡፡ ለማንኛዉም ራስ መኮንን የሰሩትን ሁሉ የሰሩት የእስልምና ሃይማኖትን ንቀው ወይም ጠልተው እንዳልሆነ የዛሬ የአደሬ ምሁራንም ፖለቲከኞችም ጠንቅቃችሁ ታዉቃላችሁ፡፡

 

ከዚህ በተጨማሪ ጊዜ ወስዳችሁ ተረት ተረት ሳይሆን ታሪክ ብታነቡ የሚከተለዉን ትገነዘባላችሁ፡

 

  • የሐረር ራስ ገዝ አስተዳደር ሲቆም ሲወድቅ ቆይቶ ሙሉ ለሙሉ የፈረሰው ግብፆች ሐረርን ሲቆጣጠሩና የወቅቱን አሚር ሙሐመድ አሊ አብዱል ሸኩርን ሲገድሉት ነበር፡፡ እናንተ ግን አስር ዓመት እንደ ባርያ ሲያንገላታችሁ ኖሮ የተመለሰዉን የግብፅ ጦር ገና ለገና እስላም ነው በሚል አንዲት ቀን እንኳን ለመዉቀስ ሲዳዳችሁ አይታይም፡፡ ይልቁንም እጅግ ትሁት እና ደግ የነበሩትን ራስ መኮንንን ገና ለገና ክርስቲያን ናቸው ወይም የጣሊያን ባንዳ ልጆች ቡድን የሆነው ህወሓት ይጠላቸዋል ብላችሁ ይህን ያህል በሌሉበት ዘመን መዉቀሳችሁ ምስጋን ቢስ መሆናችሁን ያሳያል፡፡
  • ሌላው መጥፎ ዜና አሁን የሐረር ምልክት አድርጋችሁ በየቦታዉ የምትለጥፉት የህንፃ ንድፍ የራስ መኮንን የህንፃ ግንባታ ባለሙያዎች ንድፍ ነው፡፡ በሐረር የኖረው የቤት ሥራ ልምድ ልክ እንደ አርጎባዎች አይነት ሲሆን አሁን የሐረር ምልክት የሆነው የህንፃ ንድፍ ከህንዶች የተወሰደ ነው፡፡ የአሚር አብዱላሂ ወይም የጣሊያን አደለም፡፡ ከራስ መኮንን በፊት ሐረር ከተማ ዉስጥ የነበሩት ጎጆ ቤቶች እና የተወሰኑ ግብፆች የሰሩዋቸው አሁን ያሉት አይነት የስሚንቶ ቤቶች ናቸው፡፡

በመጨረሻም ሐረርን አሁን ከደረሰችበት ደረጃ ላይ ሆኖ ወደ ኋላ እየተመለከቱ እነ ራስ መኮንንን መዉቀስ እርስ በርሱ የሚጋጭ ቅዤት ነው፡፡ ራስ መኮንን እና የሳቸው ልጆች እና የልጅ ልጆች የገነቡት ከተማ ላይ ነው ዛሬ የማንም ጎሰኛ እና ፈሪ የሚዘልበት፡፡ የሚያሳዝነው ይሄ ዛሬ እየለኮሳችሁት ያለው እሳት ሳይዉል ሳያድር እናንተኑ እንደሚያቃጥላችሁ አለመረዳታችሁ ነው፡፡ የጎሳ እና የሃይማኖት ፅንፈኝነት መቆሚያ የለዉም፡፡ ዛሬ ጠላት ክርስቲያን ነው፡፡ ነገ ደግሞ ኦሮሞ ይሆናል ወይም አደሬ ይሆናል፡፡ ዛሬ አንዱ አዝኖ ወይም ሞቶ ይሆናል፡፡ ነገ ግን ሌላው እንደሚያዝን እና እንደ ሚሞት አለማሰብ ድንጋይነት ነው፡፡ የሰራችሁትን እብደት እና የዘራችሁትን ዉሸት መሰብሰብ የማትችሉበት ቀን ይመጣል፡፡ የዛን እለት እናንተን አያድርገኝ!!

 

ክፉን ከደግ የምትለዩበት አእምሮ ይሰጣችሁ ዘንድ ቸሩ መድኃኒተአለምን እለምናለሁ!!

ግርማ ተ. ካሴ

ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓም ተፃፈ