ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ትውልዶች ዓይነተኛ ልጅ

ውድ የአሥራት ሚድያ ቤተሰቦችና ወዳጆች፤ እንዲሁም ወንድምና እህት ኢትዮጵያውያን፤
እንደሚታወቀው፤ ዛሬ ግንቦት ፮ ቀን የሚድያችን መጠሪያ ስም ባለቤት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ከዚህች ዓለም በሞት የተለዩባት ቀን ናት።
ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ትውልዶች ዓይነተኛ ልጅ፣ በአርዓያነት ለዘላለም ሲጠቀሱ ከሚኖሩ ጥቂት ሀገር ወዳዶችና ጀግኖች አንዱ ናቸው። ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለፍትህ፣ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለዜጎች እኩልነትና ለነጻነት፤ ከራሳቸው ዝና፣ ክብርና ጥቅም በላይ ለሀገራቸውና ለወገኖቻቸው የጋራ ጥቅም ታግለዋል። ለቆሙለት ዓላማም እስከመጨረሻይቱ እስትንፋሳቸው ድረስ ጸንተዋል፤ ታምነዋል። እንደቀደምቶቹ ጀግኖቻችን በደስታና በኩራት እስከወዲያኛው አሸልበዋል።
ወልዳ ያሳደገቻቸውን ሀገር ክደው፣ ሽጠው፣ ሸንሽነውና አበጣብጠው በመጨረሻም ለዘላለሙ የተረገመ ስም ይዘው እስከወዲያኛው ለተሰናበቱት ገዳዮቻቸው ይብላኝላቸው እንጂ፤ አስራት ወልደየስ ስማችው ከመቃብር በላይ ውሏል።
በክብር ስላለፉት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ይህንን ካልን፤ ወደኛው ትውልድ ደግሞ እንመለስና፤ በውነት ከታላላቅ ጀግኖቻችን ምን መማር እንችል ይሆን? ምንስ ማስቀጠል እንችል ይሆን? ቀደምት ትውልዶች ያልነበሯቸውን ዘመናውያን የጥበብ ፀጋዎች ተጠቅመንስ ምንን ማሻሻል እንችል ይሆን? ለቀጣይ ትውልድስ ምን ማውረስ እንችል ይሆን? ስናልፍስ ምን ውርስ ጥለን ማለፍ እንችል ይሆን? ሁላችንም ራሳችንን እንጠይቅ! ውስጣችንን እንፈትሽ!
ከላይ ካነሳናቸው ጥያቄዎች በተጨማሪ፤ ባለትልቁን ስም ሚድያችንንስ ለማስቀጠል ምን ማድረግ እንችል ይሆን?
መልካም የመታሰቢያ ዕለት ይሁንላችሁ፤ ይሁንልን!
ድር ቢያብር፤ አንበሳ ያስር!
የአሥራት ሚድያ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ።
ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *